ማየት የተሣናቸው ሠዓሊዎች

ግጥሞች፣ታሪኮች፣ፎቶዎች፣ሙዚቃዎች
Poems,Short stories, graphics,pictures,musics,Technology
User avatar
morefun
Leader
Leader
Posts: 152
Joined: 06 Sep 2009 01:52
Contact:

ማየት የተሣናቸው ሠዓሊዎች

Unread post by morefun » 06 Oct 2009 01:25

Image

Image

እንዲሁ በሃሳቧ ስዕል ትወዳለች፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ስዕሎች ሲያጋጥሟት አጠገቧ የሚገኙን ሥዕሉ ምን እንደሆነ በማለት በተደጋጋሚ ጠይቃለች፡፡ መክሊት ድሪባ አንድ የምታውቀው ሰው ማየት የተሳናቸውን ስዕል ለማሰልጠን በዝግጅት ላይ ያለች ወጣት አርቲስት መኖሯን ሲነግራት የስልጠናው ተሳታፊ ለመሆን አላቅማማችም ነበር፡፡

በማለቅ ላይ ባለው ዓመት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት የዲግሪ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው መክሊት ለሁለት ወር የሥዕል ሥልጠና በመውሰድ ባለፈው ሳምንት ለአራት ቀናት የስእል ሥራዎቻቸውን በብሔራዊ ቴአትር ካቀረቡ ማየት የተሣናቸው መካከል አንዷ ለመሆን ችላለች፡፡

"ስዕል ልታሰለጥን ነው ሲባል የጠበቅኩት እንደዚህ አልነበረም፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለን ክር ወይም ገመድ ነገር በማጣበቂያ ካርቶን ላይ እያደረጉ የኢትዮጵያ ካርታ ይሰሩልን ነበር፡፡ እኔም የዚያ ዓይነት ነገር ነበር የጠበቅኩት፡፡ መጀመሪያ መስመሮች፣ ክብ፣ ግማሽ ክብና ሦስት ጎን የመሳሰሉት ነገሮችን ነበር አሰልጣኟ ያሳየችን፡፡ መሥሪያዎቹን ሁሉ ስታሳየን እችለው ይሆን? ብዬ ተጠራጥሬያለሁ፡፡ በመጨረሻ ግን በሰጠችን ፎርማት መሠረት ስሞክረው መስራት እንደሚቻል አወቅኩኝ"

እይታዋን ያጣችው ከጊዜ በኋላ በመሆኑ ስዕል ታውቃለች፡፡ ነገር ግን እንዴት ማስቀመጥ እንደሚቻል አታውቅም ነበር፡፡ አሰልጣኟ ስኒ፣ ኩባያና ብርጭቆ በመሳል ለሰልጣኞቹ በመስጠት በሚገባ መስመሮችን በመዳሰስ እንዲያስተውሉት፤ ከዚያም ኮፒ እንዲያደርጉት ማድረጓ በሚገርም ሁኔታ እንደረዳቸው መክሊት ነግራናለች፡፡ ስልጠናው ላይ የነበራትን ነገር በማስመልከት ደግሞ የሚከተለውን ብላለች፡፡ "አይን ሥትሥልልኝ መጀመሪያ ቅንድቡን ብቻ፣ ከዚያ ከላይ ያለውን ቆብ በመጨረሻም ብሌኑን ለብቻው እንድትሥልልኝ እጠይቃት ነበር፡፡ በዚህ መልኩ እሷ የሰራችውን ሥዕል ኮፒ በማድረግ መሣል ተለማመድን፡፡"

እይታዋን ያጣችው ከጊዜ በኋላ በመሆኑ የተወሰነ ስነ ስዕላዊ እይታ መያዟ ለዛሬው የሥዕል ሥልጠናና ሥራዋ አስተዋጽኦ ይኖረው እንደሆነ መክሊትን ጠየቅናት፡፡ "ምሥልን ማወቅና መሣል የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን መገንዘብ ችያለሁ፡፡ ቀደም ሲል ስለ ሥዕል እንዲያስረዱኝ የምጠይቃቸው ሰዎች ይነግሩኝ የነበረው በሥዕሉ ስለሚታየው ነገር ነበር፡፡ ለምሳሌ ሴትና ወንድ ናቸው፣ እንደዚህ እያደረጉ ነው፣ የዚህ ዓይነት ልብስ ለብሰዋል በማለት ሥዕሉን ሊገልፁልኝ ይሞክሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ስለ ሥዕል የነበረኝ አእምሮአዊ ምስልና ስዕል መሳል የተለያዩ ሆነው ነው ያገኘኋቸው" በማለት መልሳልናለች፡፡

ማየት የተሣናቸው ሊስሉበት የሚያስችለው ፕላስቲክ ወረቀት ላይ የተቀመጡ ሥዕሎችን በመዳሰስ መገንዘብ ለመክሊትና ለጓደኞቿ ብዙም ከባድ አልነበረም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን የተወሰኑ ነገሮችን ትዘነጋ ስለነበር አሰልጣኟ ድጋሚ አንድታሳያት ትጠይቃት ነበር፡፡

ማየት የተሣናቸው የሥዕል ሰልጣኞች የሥዕል ስራዎች በቀረቡበት ኤግዚቢሽን ላይ የተለማመዱባቸው በርካታ ፕላስቲክ ወረቀቶችም ለህዝብ ታይተው ነበር፡፡ የልምምድ ጊዜዋን በማስታወስም "በፕላስቲክ ወረቀቶቹ ላይ የሣልኳቸው ሥዕሎች ችግሮች ነበሩባቸው፡፡ አይን ወደ ግንባር ይጠጋብኛል፣ አፍንጫና አይን ይሰፋብኛል ወይም ጆሮ ይተልቅብኛል፡፡ ደህና ሰራሁ የምለው ቀለም መቀባቱን ነው፡፡ መጀመሪያ ላይ ሳስብ ግን ከብዶኝ ነበር፡፡ ግን ቀለሙ እርጥበት ስላለው እርጥበቱን በመዳሰስ (በስሱ) እየተከተልን መቀባት ችለናል፡፡ ቀለም ነክሮ ካቆምንበት እንደገና መጀመር ግን አስቸጋሪ ሆኖብን ነበር፡፡ ጣቶቻችን ላይ ያለው ቀለም እዚህም እዚያም ይለቀለቅብናል" ብላለች፡፡

ባለፈው ሳምንት በብሔራዊ ቴአትር ለአራት ቀናት የቆየው ማየት የተሣናቸው የሣሏቸው ሥዕሎች ለእይታ በቀረበበት ኤግዚቢሽን አሰልጣኟ ወጣት ሰብለ ወልደ አማኑኤል ሥራዎችም ቀርበው ነበር፡፡ መክሊትም በሥራና በትምህርት የምታውቃቸውን በሥዕል ኤግዚቢሽኑ ላይ በመገኘት የሥዕል ሥራዋን እንዲመለከቱላት ጋብዛ ነበር፡፡ "በፕላስቲክ ወረቀት ላይ የተሰሩ ሥዕሎቻችን ላይ ምንም ዓይነት ጥያቄ አላነሱም፡፡ በሸራ ላይ በቀለም የተሣለውን ግን ተጠራጥረዋል፡፡ አላመኑም፡፡ አልሰሩትም ግን ስለመጣን እንየው ሲሉ ሰምቻለው፡፡ ግን ጠይቀውን በፕላስቲክ ላይ የሰራነውን ሸራው ላይ ኮፒ ማድረጋችን እንዲሁም እንዴት እንደሰራነው ብንግራቸው ጥሩ ነበር፡፡ ፕላስቲኩ ወረቀት ላይ የሠራነውን አይን ሸራ ላይ መሥራት ምንም የተለየ ፎርም እንደሌለው ቢረዱ ያምኑን ነበር"

ማየት የተሣነው እንዴት ሊሥል ይችላል? የሚል ጥያቄ ለሚያነሱ "በትምህርት ይቻላል፡፡ አሁን ትንሽ ስልጠና ነው የተሰጠን፡፡ መቻላችንን አጭር ስልጠናው ማሳያ ይሆናል" ብላለች፡፡

አለማየሁ ደምስ በሥዕል ሥልጠናው ላይ ከተሳተፉ ማየት የተሳናቸው አንዱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሺዮሎጂ ሦስተኛ ዓመት ተማሪ ሲሆን፣ ለሥዕል የተለየ ፍቅር አለው፡፡ ጥቂት በማይባሉ አጋጣሚዎችም ፣መሣል ብችል፣ እያለ ተቆጭቷል፡፡ ሠዓሊ ጓደኛ ቢኖረውም መሣል ለእሱ ፈጽሞ የማይቻል እንደሆነ በማመን ስለ ሥዕል ምንም ዓይነት ጥያቄ አንስቶ አያውቅም፡፡ ሥልጠናውን ከጀመረ በኋላም አለማመኑ ቀጥሎ ነበር፡፡ "መሣሌን ያመንኩት በኤግዚቢሽኑ ላይ የተገኙ ሰዎች ይህንንማ እነሱ አልሣሉትም የሚል አስተያየት ሲሰጡ ነው፡፡ በአስተያየታቸው ተደሰትኩ፤ ደህና መሄዳችንም ገባኝ"

እይታውን ያጣው ከጊዜ በኋላ በመሆኑ ልጅ ሳለ ሥዕሎችን ተመልክቷል፡፡ ከጊዜ ብዛት ግን ትውስታው ጠፍቷል፡፡ "ሥዕል ተማሩ ሲባል በማሽን መስሎኝ ነበር፡፡ የጀመርኩትም በማሽን መስሎኝ ነው፡፡ ይህ አለመሆኑን ስረዳ ያልተመለስኩት አሰልጣኟ ሃሳ/ን በማመንጨቷ በመገረሜና በመደሰቴ ነበር" ብሎናል፡፡

በመጨረሻ ለኤግዚቢሽን የቀረቡት የመክሊትና የአለማየሁ ሥራዎች በሸራ ላይ የተሰሩ የሴትና የወንድ ምስሎች ነበሩ፡፡ አለማየሁም አፍንጫ መሳል በጣም ያስቸግረው እንደነበር ይህ የሆነውም በእጁ ሲዳስሰው (ምስል ላይ) ቅርፁ ሊመጣለት ባለመቻሉ እንደሆነ አጫውቶናል፡፡

ሥዕል መሳል እችላለሁ ብሎ ባለማመኑ የሁለት ወር ሥልጠና ሲወስድ አንድም ቀን ለማንም ተናግሮ አያወቅም፡፡ በመጨረሻ ቀን ግን ሥዕሉን እንዲመለከቱለት የጠራቸው ጓደኞቹ የሰጡት አስተያየት አበረታች ነበር፡፡ ማየት የተሳናቸው መሣል መቻላቸውን ለማያምኑ "የግድ ሥዕል በእስክሪብቶ መሆን የለበትም፡፡ ማየት የሚያመጣው ትክክለኛነት ሙሉ በሙሉ ባይጠበቅም መሣል እንደምንችል ማረጋገጥ እንችላለን" ብሏል፡፡

ሲጀመር አስራ ሁለት ከዚያም የቀሩትን ሰባት ማየት የተሳናቸው ለሁለት ወራት ሥዕል መሣል ያሰለጠነችው ወጣት ሰብለ ወልደ አማኑኤል ትባላለች፡፡ በአንድ የግል ትምህርት ቤት የሥዕል መምህር ነች፡፡ በተለያዩ ጊዜአት የሥዕል ሥራዎቿን ለእይታ ስታቀርብ ማየት የተሳናቸው የቅርብ ጓደኞቿ የዘወትር "እኛስ ስራሽን መቼ ነው የምናየው?" ጥያቄ የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ ማየት የተሳናቸውን የሚያሳትፍ አንድ ሥራ መሥራት እንደሚገባት አሳሰባት፡፡ ለዓመታት ሁኔታውን ስታወጣ ስታወርድ ቆይታ ማየት የተሳናቸው ሊሥሉ የሚችሉባቸውን ቁሳቁስ ለመፈለግ መንቀሳቀስ ጀመረች፤ ተሳካላትም፡፡

በሥልጠናው ላይ የተሳተፉትን ማየት የተሳናቸው ያገኘቻቸው በምታወቃቸው የተለያዩ ሰዎች ሲሆን የመረጠቻቸውም ለሥዕል ያላቸውን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ነው፡፡ "መጀመሪያ ላይ አስራ ሁለት ነበሩ፡፡ እንዴት እንችላለን በማለት መጨረሻ ላይ የቀሩት ሰባት ብቻ ናቸው፡፡ ለሁለት ወራት እንደ ስሜታችን በቀን ለሁለት ሰዓታት ስንለማመድ ቆይተናል"፡፡

ስልጠናው የተጀመረው መስመር ከመሳል እንደሆነ የምትናገረው ሰብለ ማየት የተሳናቸው ቢሆኑም የሥዕል ፍላጎት ካላቸው ውስጣቸው ያለው ነገር በአካባቢ ተጽዕኖ ሊቆይ ይችል ይሆናል እንጂ እድሉ ከተገኘ ለአንድ አፍታ እንኳ ብልጭ ብሎ መውጣቱ እንደማይቀር ታምናለች፡፡ "አለማየት የሚከለክለው ቀለምን እና ፎርምን ነው፡፡ ሌላ ውስጣዊ ነገርን የሚከለክል አይመስለኝም"

ስልጠናውን ለመስጠት ስትነሳ አዎንታዊም አሉታዊም አስተያየት ተሰጥቷታል፡፡ ሰብለ "ምን አደከመሽ ያሉኝም" ነበሩ ብላናለች፡፡ በስዕል ኤግዚቢሽኑ ላይ የቀረቡትን በፕላስቲክ ወረቀትና በሸራ የተሰሩ የቅብ ስራዎችን በማስመልከት በተመልካቾች የተለያዩ አስተያየቶች በጽሁፍ መሰጠታቸውን፤ ሰብለ "ማየት ከንቱ የሚል" አስተያየት ተጽፎ ማንበቧን ነግራናለች፡፡

ቀለም በመምረጥ፣ በመንከርና ከዚህ እስከዚህ በማለት ቅብ ላይ እንደረዳቻቸውም ገልጻልናለች፡፡

"አርት ብርሃን ብቻ አይደለም፡፡ በአካባቢያችን ያለውን ቁስ አካል በመግለጽ ሃሳባቸውን መግለጽ የሚችሉበትን ሁኔታ ማየት ለተሳናቸው ብንፈጥርላቸው ትልልቅ አርቲስቶችን ማፍራት ይቻላል" ያለን በኤግዚቢሽኑ መዝጊያ እለት ከቦታው የተገኘ አንድ ተመልካች ነው፡፡

Image


Post Reply

Return to “Ethio Art and Culture..ኢትዮ ጥበብ ፤ስነ ጽሁፍ ፤”