ኬላና ቀረጥ ውሳኔ

ግጥሞች፣ታሪኮች፣ፎቶዎች፣ሙዚቃዎች
Poems,Short stories, graphics,pictures,musics,Technology
User avatar
selam
Leader
Leader
Posts: 175
Joined: 25 Aug 2009 01:59
Contact:

ኬላና ቀረጥ ውሳኔ

Unread post by selam » 09 Jun 2010 22:00

ኬላና ቀረጥ ውሳኔ

ዐፄ ኢያሱ በዘመናቸው ጣልቃ እየገባ ከሚደረገው ጦርነት በቀር በተረፈ አገሩ ሰላማዊ በመሆኑ እርሻና ንግድ በጣም ተስፋፍቶ ነበር፡፡ በዚያ ጊዜም ከስናር ከካይሮ ከምጥዋ ብዙ ሸቀጥ ወደ ጐንደር ወደ ሌሎችም አውራጃዎች እየገባ እንደዚሁም ከጐንደርና ካውራጃው እህል፣ ቅቤ፣ ቡና፣ ቆዳ፣ ከብት ወደ ውጪ እየወጣ ይሸጥ ነበር፤ ንጉሡ ዐፄ ኢያሱም የወግና የሥርዓት ደንብ ለማበጀት ከመጣራቸው ጋር የንግዱም ጉዳይ በደንብ እንዲሆን ይጥሩ ነበር፡፡ ስለዚህ ንግዱ በኬላና በቀረጥ ነበር፡፡ ስለዚህ ንግዱ በኬላና በቀረጥ ብዛት እንዳይቸገር አስበው ከዚህ ቀጥሎ ያለውን የቀረጥ ደንብ ካማካሪዎቻቸው መክረው ዐወጁ፡፡

1ኛ ባንድ አውራጃ አንድ ኬላ ብቻ እንዲሆን፣
2ኛ ባ5 በቅሎ ጭነት አንድ አሞሌ ጨው እንዲከፍል፣
3ኛ በ8 አህያ ጭነት አንድ አሞሌ ጨው እንዲከፍል፣
4ኛ በትከሻ የሚነግደው ቀረጥ እንዳይከፍል፣
5ኛ በጐንደር መካከል ባለው ገበያ የሚውለው የበግና የፍየል ነጋዴ በጭራሽ ድላል (ቀረጥ) እንዳይከፍል አደረጉ፡፡

(የኢትዮጵያ ታሪክ፤ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣1949)

ሰባኪው ወፍ

በእንግሊዝ አገር፣ ማንቼስተር በተባለው ከተማ ወደሚገኝ አንድ ቤተክርስቲያን በየዕለተ ሰንበት ምዕመናን ይጎርፋሉ፡፡ ከቤተክርስቲያኑ አስተዳደር ትከሻ ላይ ቁብ ብሎ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የሚያነበንብ "ቻርሊ" የሚባል ወፍ አለ፡፡ ቻርሊ በቀቅ ፓሮት የሚሰኘው ወፍ ዝርያ ነው፡፡ በቀቆች እንደ ቴፕሬኮርደር የሰሙትን ድምፅ መልሰው የማስተጋባት ልዩ ተፈጥሮዋዊ ችሎታ አላቸው፡፡ በመሆኑም ቻርሊ፣ ካህኑ የሚሉትን ሁሉ፣ እየተቀበለ ለምዕመናን ያስተጋባል፡፡ የማስታውስና የመደጋገም ባህርይም ስለአለው ካህኑ ዝም ባሉበት ወይም እስካናካቴው በሌሉበት ወቅት እንኳ ቻርሊ የሚለው አያጣም፡፡ "እግዚአብሔር ይወደኛል"... "እግዚአብሔርን አመስግኑ"... ይላል፡፡

"የሰማትን ቃል አይረሳም" በማለት ያወድሱታል፣ ባለቤቱ ብጹዕ ሎወሬንስ ብራድሊ፡፡ "በዝማሬም የሚያጅበኝ ጊዜ አለ፡፡ ከአንዳንድ አጐል ቄስ እርሱ ይበልጣል ብዬ እገምታለሁ" ብለዋል፡፡

በቀቅ የብልግና ቃልም ከሰማ ያንኑ መልሶ ከመወርወር አይታቀብምና በስብከቱ መሀል ጣልቃ እንዳያስገባው፣ ያውም ቤተጸሎት ውስጥ የሚሰጉም አልታጡም፡፡ "አይዟችሁ....ይላሉ ብፅዕ ሎውሬንስ ብራድሊ፤ ..ፀያፍ ቃል አይወጣውም፡፡ እንዲያ ያለ ጋጠወጥነት በአካባቢያችን መች ይኖርና.... በማለት ምዕመናኑን ያፅናኗቸዋል፡፡

የሰይጣን ጆሮ አይስማ እንበል፡፡

(ከዓለም አስደናቂ ዜናዎች፤ትንግርት መፅሔት፣)

በራስ መተማመን


አብዛኛውን ጊዜ "ለራስ መልካም አመለካከት መያዝ" እና "በራስ የመተማመን ስሜት" የሚሉት አነጋገሮች ተመሳሳይ እንደሆኑ ተደርገው ይነገራሉ፡፡ ግን አይደሉም፡፡ ለራስ መልካም አመለካከት መያዝ ለማንም ሰው የበለጠ አስፈላጊ ነገር ነው የራስ ምስል ነፀብራቅ ነውና፡፡ በተጨማሪም ለራስ መልካም አመለካከት መስጠት፣ ከሰው ጋር አብሮ የሚወለድ ነገር አይደለም፡፡ በአብዛኛው ከወላጆች፣ ከመምህራን ከዘመዶችና ከምንኖርበት ኅብረተሰብ የሚሰጥ ስጦታ ነው፡፡ በራስ መተማመን ደግሞ ጥቂት ለራስዎ ያለዎት መልካም አመለካከት በስጦታ መልክ ካገኙ በኋላ፣ ጥቂት ጥረት በማድረግ የሚያገኙትና የሚያዳብሩት ባህርይ ነው፡፡

ስለዚህ አንድ ሰው በራሱ አይተማመንም ስንል፣ ዘወትር ከሚያደርጋቸው ድርጊቶቹ አንፃር አይተን የምንወስደው አቋም ነው ማለታችን ነው፡፡ "መዝፈን እችላለሁ"፣ "ውድድር ውስጥ እሳተፋለሁ"፣ "ይህን ብስክሌት መጋለብ አያቅተኝም"፣ "መዋኘት አውቅበታለሁ"፣ ወይም "ይህንን ሬዲዮ ልጠግነው እችላለሁ" የሚሉት አባባሎች የሚመነጩት ከራስ የመተማማን መንፈስ ነው፡፡ እርስዎም በራስ የመተማመን ስሜት ካለዎት በተወሰነ ደረጃ ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለራስዎ ያለዎት መልካም አመለካከት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ካልደረሰ ግን በምንም መልኩ ደስተኛ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ለራሱ ጥሩ አመለካከት የሌለው ሰው ሚሊየነር ወይም የብዙ ኩባንያዎች ሥራ አስከያጅ እንኳ ቢሆን፣ ውስጡ ሰለም ተሰምቶት ህይወትን በደስታ ሊያጣጥማት አይችልም፡፡ ለራሱ ጥሩ አመለካከት ያለው ሰው ግን ጤነኛ ከሆነ እና ለኑሮው አስፈላጊ የሆኑትን ጥቂት መሠረታዊ ነገሮችን ብቻ ከተሟሉለት ደስተኛ ሆኖ ህይወትን ሊያጣጥም ይችላል፡፡ እርስዎ ስለራስዎ ጥሩ አመለካከት ካለዎት መልካም ጤንነት ይኖርዎታል፣ በተለይም የአዕምሮዎ ጤንነት የተጠበቀ ይሆናል፡፡

ለራስዎ ያለዎት ጥሩ አመለካከት እጅግ አናሳ ሆኖ በተጨማሪም በራስ የመተማመን ስሜት ከሌለዎት ግን ውጤታማ ለመሆን በጣም ያስቸግርዎታል፡፡

(የስኬታማ ሰው ባህሪያት፤ዶ/ር ኖርማን ቪንሰንት ፔል..ማኅሌት ጥላሁን..፣1999)

ገራገር
ለማስታወቂያነት በቀን መቁጠሪያ ላይ የወጡ ምስሎች ተቃውሞ ገጠማቸው


በጀርመን አገር ከውድቅዳቂ ቆሻሻዎች የተሰሩትን ልብሶች በቀን መቁጠሪያ ላይ በሞዴሎች ለማስተዋወቅ የተደረገው ሙከራ ተቃውሞ ገጠመው፡፡

ከውድቅዳቂ ቆሻሻዎች የተሰሩት የጡትና የሃፍረተ ስጋ መሸፈኛ ልብሶች በጣም ስስ ከመሆናቸውም በተጨማሪ፤ ለባሾቹ ልጃገረዶች ቀሪ የሰውነታቸውን ክፍል ራቁታቸውን በመሆናቸው ተቃውሞ ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡

በቤት ውስጥ የሚጠቀሙባቸውን እቃዎች በድጋሜ ወደ መጠቀሚያነት መቀየር እንደሚቻል ለማሳየት መሆኑን አምራቾቹ ቢናገሩም፣"እንደዚህ ያለ ነገር መጠቀም ፋብሪካውም ቆሻሻ መሆኑን ያሳያል" ሲሉ ተቃዋሚዎቹ ተናግረዋል፡፡

ቆንጆዎቹ በውፍረት ምክንያት ከአባልነታቸው ተሰረዙ

ዴቲንግ ዌብ ሳይት ዶት ኮም የሚባለው የቆንጆዎች መገናኛ ድህረ ገጽ በገና በዓል ምክንያት ክብደታቸው የጨመረ አምስት ሺ አባላትን መቀነሱን ዴይሊ ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡

ቆንጆዎቹ ፎቶግራፋቸውን በድህረገጹ ሲልኩ መጠናቸው (ውፍረታቸው) በጣም በመጨመሩ "ስትስተካከሉ በድጋሚ አባል መሆን ትችላላችሁ" በሚል ሊሰረዙ ችለዋል፡፡

አብዛኛዎቹ የድህረ ገፁ ደንበኞች ከአሜሪካና ካናዳ ሲሆኑ ከእንግሊዝ 900 የሚሆኑ ደንበኞች የድህረ ገፁ አባላት መሆናቸውን ዴይሊ ቴሌግራፍ ዘግቦ በየጊዜውም በመቀጣጠር እንደሚገናኙም አሳውቋል፡፡ በገና በዓልና በአዲስ ዓመት በሚያገኙት እረፍት ቁጭ ብለው በርካታ ምግብ ስለሚመገቡ ውፍረታቸው ከሚፈለገው በላይ እንደሚጨምርም ገልጿል፡፡

በፖሊስ መኮንኑ ቢሮ የዓይጥ መሸሸጊያ ተገኘ


በእንግሊዝ አገር የአይጦችን ወረራ ለማጥፋት የተሰማሩ የፖሊስ አባላት በአንድ የፖሊስ መኮንን ዴስክ ሥር የዓይጥ መኖሪያ አገኙ፡፡

የተለያዩ ነፍሳትን ለማጥፋት በኬንግተን የተቋቋመ ቢሮ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመያዝ በከተማው ውስጥ የሚገኙትን ዓይጦች ለማጥፋት የታዘዙት ፖሊሶች በመጀመሪያ ፍለጋቸውን በፖሊስ መኮንኑ ቢሮ በማድረጋቸውና የዓይጥ መሸሸጊያ ማግኘታቸው አስገርሟቸዋል፡፡

እንደ ዴይሊ ቴሌግራፍ ዘገባ፣ አይጦቹ በፖሊስ መኮንኑ ቢሮ በዴስክ ሥር በወረቀት የሠሩት መሸሸጊያ በፅዳት ሠራተኞች በየቀኑ ቢፀዳም ሊጠፋ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

ሜት የሚባሉት ቃል አቀባይ "ነገሩ የሚያስገርም ቢሆንም አይጦቹ በወረቀት የሠሩት ቤት በአንድ ፖሊስ መኮንን ዴስክ ሥር መገኘቱ ከፖሊስ ሥራ ጋር የሚያገናኘውና ችግር የሚፈጥርም አይደለም" ብለዋል፡፡

የዓለም አጭሩ እና ረዥሙ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኙ

ስምንት ጫማ ከአንድ ኢንች ርዝማኔ ያለው ሱልጣን ኮስን እና ሁለት ጫማ ከአራት ኢንች እርዝማኔ ያለው ሰው ፒንግ ፒንግ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ምንም እንኳን ሁለቱ ሰዎች ከፍተኛ የቁመት ልዩነት ቢኖራቸውም በጣም ብዙ የሚያመሳስሏቸው ነገሮች እንዳሉ ተገልጿል፡፡

ሁለቱ ሰዎች የተገናኙት በኢስታንቡል የወርልድ ጊነስ ሪከርድስን መክፈቻን በማስመልከት ነው፡፡

የዓለም ረዠሙ ሰው ቶኪዮ ከተማ ከረገጥኩበት ጊዜ ጀምሮ ፒንግ ፒንግን በጣም ማግኘት እፈልግ ነበር በማለት ሚስተር ኪሲን ተናግሯል፡፡

Post Reply

Return to “Ethio Art and Culture..ኢትዮ ጥበብ ፤ስነ ጽሁፍ ፤”