የኔ ጥላሁንን ገሰሰ

ግጥሞች፣ታሪኮች፣ፎቶዎች፣ሙዚቃዎች
Poems,Short stories, graphics,pictures,musics,Technology
ኦሽንoc
Leader
Leader
Posts: 1129
Joined: 07 Aug 2009 14:20
Contact:

የኔ ጥላሁንን ገሰሰ

Unread post by ኦሽንoc » 08 Apr 2010 13:30

የኔ ጥላሁንን ገሰሰ

(ከቢሌ)

ያን ሰሞን ንጉሱ ከዚህ አለም የተለየ ጊዜ ፤“ጥላሁን ሞተ” ማለት አሁንም ይከብደኛል፤እኔም የበኩሌን ልል
ፈለግሁና ትራፊኩ በዛብኝ ፤ብዙ አድናቂዎቹ ስለሱ ብዙ ይሉ ነበር እና ነው ይሄን ማለቴ ፤ሃዘኔን ግን ብቻየን ነው
የተወጣሁት ፤ለጥላሁን እልፈት አለቀስኩ ብል ቀላል ቃል የተጠቀምኩ ነው የሚመስለኝ፤አነባሁት ፤እዬዬን
አስነካሁት፤ጨርቄን ጣልኩ ብል አሁንም ተቀራራቢ የሃዘን መግለጫ አይመስለኝም።ግን የሆነው ሆኗል፤ ኢትዮጵያ
አልፎም አፍሪካ አንድ ልጅ አጣች ፤ድምፁ ወደር የማይገኝለት አንጋፋው የኢትዮጵያ የኪነት አባት ጥላሁን ገሰሰን
ከሁላችንም እጅ አመለጠ ።

ጥላሁንን እኔ ሳውቀው፤
አንደኛ ታሪክ።
በልጅነት ጊዜ
1960 መጀመሪያ ላይ እኔ ልጅ ነበርኩ ፤ከተወለድኩበት ከፍልወሃ ወደ ሾላ ቤት ቀይረን የገባን ሰሞን አንድ እሁድ
ጠዋት አባቴ “ቅመም” ዛሬ ከኔ ጋር ነው የምትውለው አለኝ፤ልጅ ሆኜ አባቴ ቅመም እያለ ነበር የሚጠራኝ፤ያን
እሁድ ጠዋት እናታችን ወ/ሮ ጥሩነሽ ተዝቆ ከማያልቀው ሙያዋ የዘሮቿን የቂጣ ፍርፍር ሰርታልን እኔና አባቴ ያንን
በሻይ እያጣጣምን ከበላን በኋላ አባቴ ጋር ተያይዘን ከቤት ወጣን።
ከቤት ወጥተን በጀነራል አቢይ ቤት በኩል አድርገን ዛሬ ያ ግቢ እስራኤል ኤምባሲ ሆኗል በሱ ግቢ አልፈን፤በፊት
የጣሊያን መሳሪያ ግምጃ ቤት ኋላ ላይ ንጉሱ አካለስንኩላን እራሳቸውን እንዲረዱበት እና የስጋጃ ምርት
እንዲያዘጋጁበት ባዘጋጁላቸው ትልቅ መጋዘን ፊት ለፊት መንገዳችንን ይዘን በወ/ሮ ዘርፈሽዋል ትምህርት ቤት ጓሮ
ስንደርስ ነው አባቴ ዛሬ አባባ ጃንሆይን ታያለህ ያለኝ።
አባባ ጃንሆይ ያን ቀን እዚያ ሰፈር የመጡት እሳቸው አባት ሆነውላቸው በስማቸው የሚጠሩትን ልጆች ቤት
ለመመረቅ ነበር ፤ግቢው “የበጎ አድራጎት ግቢ” ይባላል፤ያ ግቢ በጊዜው ለዚያ ሰፈር እንደ “ላንድ ማርክ” ከሩቅ
የሚታይ የነበረ ሲሆን ኋላ ላይ አሚቼ የመኪና መገጣጠሚያው ሌሎችም እንደ አንበሳ ጋራጅ ወይም ደረጃ መዳቢ
ድርጅት ፎቅ ሲሰሩ የግቢውን ትልቅነት አሳንሶታል ፤ በዚያን ዘመን ያ ሰፈር ጫካ ሲሆን ፤ዛሬ ኢምፔርያል ሆቴል
ተሰርቶለት የገርጂ መንገድ በዚያ በኩል ወጥቶለት አራዳ ከመሆኑ በፊት ፤በጊዜው የቀበጡ መኳንንት እስቲ ድኩላ
አድነን እንምጣ የሚሉበት ጫካ ነበር ።
የወ/ሮ ዘርፈሽዋል ሰይፉን ትምህርት ቤት አልፈን፤ አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ መጥቶ ቤቱን የሰራበት ሜዳ ላይ
ስንደርስ ፤የኢትዮጵያ ባንዲራ ከዚያ ጀምሮ በኮረኮንቹ መንገድ አዲስ በገባው የስልክ እንጨት ላይ ተሰቅሎ እያየን
ለንጉሱ ክብር የቆመው የሙዚቀኛ ባንድ የሚመታው ማርሽ ድንገት ጆሮየ ውስጥ የታምቡሩ ጩሀት መስማት
ጀመረ።

አባቴ አቶ ታደሰ እጄን ይዞኝ ነበር የምንሄደው፤ሁኔታው አሁን ሳስበው እንደህልም ነው የሚታየኝ፤ስሜቴ ግን
አገር የሚለው ትልቅ ነገር ባንዲራ የሚባለው የሁላችንም ምልክት ያኔ የነበረው ስሜቱ ከአሁኑ የሚበልጥ
ይመስለኛል፤ያን ቀን እኔና አባቴ እዚያ ቦታ ላይ የተገኘነው አባቴ ተጋብዞ ይሁን ወይም ጠቅላላ የመንደሩ አባወራ
የሚፈልግ እንዲመጣ ተነግሮ አላውቅም ትልቁ የበጎ አድራጎት በሩ ላይ ስንደርስ የንጉሱ ጋሻ ጃግሬዎች ረጃጅሞቹ
ክብር ዘበኞች ወዲያ ወዲህ ይላሉ ፤ኋላ ላይ ደርግ ፤ወይም የዛሬው መንግስት እንደሚያደርገው ፍተሻ ብሎ ነገር
የለም ።እናቶች የክት ልብሳቸውን ለብሰው ለፀሃዩ ብለው ነጠላቸውን ከለል አርገው የተዘጋጀላቸው ቦታ ላይ
ተቀምጠዋል ፤አንዳንድ ዘመናዊ ሴቶች ፓሪ ሞድ የሚባለው ቅድ ቀሚስ አድርገው እሱኑ ፋሽን ለማሳየት ለስላሳ
እና ውሃ በየቦታው ያድላሉ ፤የጃንሆይ ልጆች የሆኑት ህፃናት ንፁህ የሆነ ሰማያዊ ሽሚዝ ከነጭ ስካርፕ ጋር
አድርገው አባባ ጃንሆይ ግርማዊ የሚለውን መዝሙር ይዘምራሉ ።
እነዚህ ልጆች አባት እናት የሌላቸው ሲሆኑ ንጉሱ እኔ አባት እሆናቸዋለሁ ብለው ከየቦታው አስለቅመው
ያመጧቸው ናቸው ፤ከነዚህ ልጆች መሃል ዛሬ ትልልቅ የህክምና ባለሙያ የሆኑ ሲኖሩ፤ በውትድርናውም በኩል
አኩሪ ተግባር ፈፅመው ያለፉ ምርጥ መኮንኖች የነበሩ እንዳሉ አውቃለሁ ፤ስም መጥራቱ ለጊዜው አስፈላጊ
አይደለም ፤እውነታው ግን መሪ እንደዚህ እታች ወርዶ ሲያስብ ነገ አገር የሚገነቡ አገር የሚጠብቁ ብቁ ዜጎች
ማፍራት እንደሚቻል ነው ፤ዛሬ እንደሚደረገው ፤የጎዳና ተዳዳሪዎች ወይም አደገኛ ቦዘኔዎች እያሉ ህፃናቱን
ማእረግ እየሰጡ ማዋከብ የትም አያደርስም ለማለት ነው ።
ያን ቀን እኔ በልጆቹ ቀናሁ ፤ዛሬ ሳስበው እኔ አባት እያለኝ በነሱ መቅናቴ ፈገግ ያደርገኛል፤
አባቴ እና እኔ ቦታችን ይዘን እንደተቀመጥን ግርግሩ በዛ እና ድንገት ሰው ሁሉ ተነሳ ፤ለካ ጃንሆይ መጥተው
ኖሯል፤ጃንሆይን ከዚያ በፊት አንድ ቀን ዛሬ አስመራ መንገድ የምንለው ያኔ የጆሞ ኬንያታ መንገድ ፤ ሞንቲቢ
የሚባለው የፊያት መንገድ ሰሪ ፋብሪካ ሰርቶ የጨረሰ ጊዜ በረጅሙ ማርቸዲሳቸው ያንን መንገድ ለማየት
በሚመጡበት ጊዜ ወይም አርብ፤አርብ ድንገት መጥተው አዳዲስ አንድ ብር በሚሰጡን ሰአት ካየኋቸው በቀር
እንደዚያ ቀኑ በቅርብ ቆመው አይቻቸው ስለማላውቅ ፈዝዤ ነበር የማየው ፤ንጉሱ ወደ ተዘጋጀላቸው ቦታ ሲሄዱ
ሴቱ ተነስቶ እልልታውን፤ ወንዱ አጎንብሶ ሰላምታውን ሰጠ ።
ጃንሆይ ከነዚያ የሰማይ ስባሪ ከሚያክሉ ወታደሮቻቸው ጋር ሳያችው አጭር መስለውኛል፤ ቦታቸውን እንደያዙ
የህናቱ ግቢ ሃላፊ ንግግር አድርገው ፤ንጉሱ ለህፃናቱ አንዳንድ ሽልማት ሰጥተው እንደጨረሱ ነው ሌላውን ንጉስ
ያየሁት ።ያ ንጉስ ጥላሁን ገሰሰ ነበር ።
ይሄ ቀጠን ያለ ጥቁር ሱፍ የለበሰ መልከ መልካም ሰው ገና ወደ መድረኩ ሲወጣ ከራሳቸው ከጃንሆይ የበለጠ ሴቱ
እልልታውን አቀለጠው ፤ዛሬ ያን ቀን ምን እንደዘፈነ አላስታውስም ፤ከማስታውሰው ነገር ግን ከራሳቸው ከጃንሆይ
የበለጠ ሰው ለሱ ሲያጨበጭብ እና ሲጮህ እንደዋለ ነው ።
የዝግጅቱ ፕሮግራም አልቆ የተዘጋጀውን ፀበል ፃዲቅ በንጉሱ ተጀምሮ በኛ በተራው ሰው መስተናገድ ካለቀ በኋላ
እዚያው አመሻሽተን ወደ ቤት ስንሄድ አባቴን እንደዚህ ብየ ጠየቅሁት ።
ታዴ! ማነው ? ያ ሰውየ ….
የቱ
ሲዘፍን የነበረው ።
ጥላሁን ይባላል ..ጥላሁን ገሰሰ ነው ስሙ አለኝ።
ንጉስ ጥላሁንን ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ አይነት ነበር ያወቅሁት በዚህ አይነት ነበር ።

ጥላሁንን እኔ ሳውቀው
ሁለተኛ ታሪክ
ጉርምስና፤
በ1970 አጋማሽ ላይ ደርግ ተዝናኑ ብሎ ድንገት የፈቀደልን ይመስለኛል ፤ለወትሮ በራዲዮ የከለከለውን የፍቅር
ዘፈን ድንገት በየቲያትር ቤቱ እንዲዘፈን አደረገ ፤አንድ ሰሞን አርቲስቶቹ እየዞሩ ሲዘፍኑ ተመልካቹ አንድ ቦታ
ሆኖ ያይ ነበር።
ነገሩ እንደዚህ ነው።
መጀመሪያ ራስ ቲያትር አንድ ቡድን ያሳይ እና ያው ቡድን ወደ ብሄራዊ ትያትር ሲሄድ በዚያው ቀን ብሄራዊ
ትያትር ያሳይ የነበረው ራስ ትያትር መጥቶ ያሳያል ፤ በዚህ አይነቱ አንድ አጋጣሚ ነው እኔና ኋላ ላይ ኩባ ሄዶ
መኮንን ሆኖ ፤መጨረሻ ላይ የለም አንተ የአገር ጠላት ነህ ተብሎ የተበተነው ሰራዊት አባል የነበረው ወዳጄ እና
አብሮ አደጌ አንድ ሻምበል ጋር ራስ ቴያትር የሄድነው ፤ያን ቀን ጥላሁን እዚያ ያሳይ ነበር፤ ተመልካቹ በጥላሁን
ዘፈን እንደ እብድ ከመሆኑ የተነሳ መድረኩን ተሸክሜ ካልሄድኩ በሚል ስሜት አዳራሹ በጩሀት ሊፈርስ ምንም
አልቀረው ፤መጨረሻ ላይ የቲያትር ቤቱ ሃላፊዎች ይሄን የህዝብ ማእበል ለማቆም ይመስለኛል፤ጥላሁንን መሳምም
ሆነ መጨበጥ የሚፈልግ ሰልፍ እንዲይዝ አደረጉ፤ እና እኔ እና ሻምበሉ ወዳጄ ተራ ያዝን ፤እኔ ከሱ ቀደምኩ እና
ተሰለፍኩ።
ሁሉም እየሄደ ጥላሁን ይስማል ፤ጥቂት ገንዘብ ያላቸው ደግሞ ለጥላሁን ያልሆነ እያሉ ብር ኪሱ ሸጎጥ
ያደርጉለታል፤ ጎረምሶቹ ሴቶች ደግሞ የስልክ ቁጥርም ወይም የትምህርት ቤት አድራሻ ፅፈው ኪሱ
ይጨምሩለታል፤እኔ ተራየ ደርሶ ሄጀ ጥላሁንን ሳምኩት ፤ብዙ ዘፈን በጊዜው ቋንቋ “ቢስ” እየተባለ ይዘፍን ስለነበር
አልቦታል ገላውን ታጥቦ እንደወጣ ሰው የራሰው ሰውነቱን አንዴ እቅፍ አድርጌ አንዴ አንገቱን አንዴ ጉንጩን
ከሳምኩት በኋላ ወደ ቦታየ ስመለስ፤ ጓደኝየ የለም።ለካ እኔ የመጨረሻው እኔ እንድሆን ተወስኖ ኖሯል።
እኔ ወደ ቦታየ ስመለስ ፤ጓደኛየ ወደ መድረኩ ሲሄድ በማየቴ ምን ሊሆን ነው በማለት ደንቆኝ ስመለከት ባዶውን
መድረክ አጎንብሶ ስሞ ሲመለስ አየሁት ።
ምነው “” ምን ማድረግህ ነው? አልኩ ጓደኛየን ሲመለስ ።
ጥላሁንን ባላገኝ የቆመበትን ስሜ መጣሁዋ አለና መለሰልኝ።ይሄ ወዳጄ እኔ እስከማውቀው ድረስ የጥላሁን ሙሉ
ኮሌክሽን በካሴት እንደነበረው አውቃለሁ ።

ጥላሁንን እኔ ሳውቀው ።
ሶስተኛ ታሪክ
ጉልምስና ፤
በ1990 ዎቹ መጨረሻ ላይ ድንገት አልነበረም ቶሮንቶ የሚባል ከተማ የተገኘሁት ፤የቻልኩትን በአውሮፕላን
ግማሹን በመኪና ሌላውን በመርከብ እያቆራረጥኩ ነው እዚህ የደረስኩት፤እዚህ አሁን የምኖርበት ከተማ አንድ
ቀን ዛሬ የልጆቼ የናርዶስ እና የቅድስት እናት የሆነችውን ባለቤቴን ያን ቀን እንደመጀመሪያ ቀጠሮ “አዲስ ዴት”
ለማድረግ ቀጠሮ ይዣለሁ ፤አዲስ “ዴት” በመሆኑ እኔ አለኝ የምለውን የክት ልብሴን ለብሼ ነው
የወጣሁት፤የምሄድበትን ግን አላውቀውም ፤እዚህ ሰሜን አሜሪካ የሚቸግረው ነገር ይሄ ነው ፤እንደ አገራችን
ቆንጆ ሴት ይዞ ኮተቤ መንገድ ፤ወይም ንፋስ ስልክ መንገድ፤ ወይም ደብረ ዘይት ወይም ከከተማ ወጣ አድርጎ
አናፍሶ ፤መመለስ አይቻልም፤እዚህ የሚቻለው ነገር የታወቀ ነው፤እናም እኔም ይቺን አዲስ ሸበላ ልጅ ይዠ አንዱ
አበሻ ቡና ቤት ጥግ ላይ አስቀምጨ ይሄን ያላበው ቤክስ ቢራ እየጠጣሁ “እፈዝባታለሁ” ብየ ሳስብ ፤ጥላሁን
ከተማው ውስጥ መኖሩን እና ዌስቲን የሚባል ሆቴል ውስጥ ዘፈኑን እንደሚያሳያ እንደ ሰበር ዜና ሰማሁ ።
ጥላሁን ጋ ለምን አንገባም አልኳት ።
ውይ በናትህ- እንዴት ደስ የሚል ነገር ነው፤ “ጥሌ” እኮ ነፍስ ነው አለችኝ።
ተያዘን ጥላሁን ጋ ሄድን እሷ አንድ የሴት ጓደኛዋን ያዘች እኔም አንድ ወዳጄ የሆነ ጓደኛየን ጨመርኩ ፡አራት
ሆነን ሆቴሉ እንደገባን ጥላሁን ታጅቦ ሲመጣ አየሁት ፤ጥላሁን ሶስት አራት በሚሆኑ ጠባቂዎች ተከቧል፤እኔ
ጥላሁንን ሳየው የተሰማኝን ስሜት አሁን መግለፅ አልችልም ፤ግን ትዝ ያለኝ ነገር ቢኖር ጓደኛየ ሻምበል እሱ
ባይኖር የቆመበትን መሬት ስሜ መጣሁ ያለው ድንገት ጆሮየ ውስጥ ሽው ያለ መሰለኝ፤እናም ከዛሬዋ ሚስቴ ጎን
ድንገት ተነስቼ ሄጄ ፤
ጥሌ እኔ እወድሃለሁ አልኩት ።
እኔም እወድሃለሁ አለና እጁን ዘረጋልኝ፤እኔ ግን ሳብ አድርጌ ሳምኩት ።እሱም እንደዚህ አለ፤ ይሄኛውስ ለምን
ይቅር አለና ሌላውን ጉንጬን ሳመኝ።
ያን ቀን እኔና ባለቤቴ በጥላሁን ዘፈን ደነስን ሁለት አዳዲስ ፍቅረኞችን አንድ ላይ አያይዞ በሚያስደንሰው ዳንስ
“ቧልስ”አደረግን፤እንዴት ውብ ምሽት እንደነበር ዛሬም በደስታ አስበዋለሁ ።
በጥላሁን ምሽት የተጀመረው ጓደኝነት ዛሬ ሁለት የወርቅ ኳስ የመሰሉ እንደጠዋት ፀሃይ የሚያበሩ መንታ ሴቶች
አፍርተናል፤ንጉሱ ግን የለም ፤እናም ይሄን ሁሉ እያሰብኩ ንጉሱ የተለየን እለት አለቀስኩ ብል የሚያንስ
አይመስላችሁም ፤እዬዬን ነካሁት እንጂ ።
እባካችሁ ጥላሁን ሞተ አትበሉ ፤ዝም ብለን Thanks for the memories, so long the king እንበለው ።
ማቴዎስ ታደሰ አደራ
ቶሮንቶ፤ካናዳ

To read this with pdf click Here
pdf by ethiomedia

Post Reply

Return to “Ethio Art and Culture..ኢትዮ ጥበብ ፤ስነ ጽሁፍ ፤”