ይቆጨኛል

ግጥሞች፣ታሪኮች፣ፎቶዎች፣ሙዚቃዎች
Poems,Short stories, graphics,pictures,musics,Technology
User avatar
selam
Leader
Leader
Posts: 175
Joined: 25 Aug 2009 01:59
Contact:

ይቆጨኛል

Unread post by selam » 03 Mar 2010 21:34

ይቆጨኛል
ልጅ በነበርኩ ጊዜ ለሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ የሚያስቡልኝ ወላጆቼ ነበሩ፡፡ ሁሉንም ነገር ደግሞ ከእነርሱ መቀበል የተፈጥሮ መብት ይመስለኝ ስለነበር፥ ምንም አሳብ አልነበረብኝም፡፡ ስለሆነም “ምን እበላ ይሆን? ምን እጠጣ ይሆን? ምን እለብስ ይሆን?” የሚለው አይነት የኃላፊነት አስተሳሰብ ወደ አዕምሮዬ ገብቶ አያውቅም ነበር፡፡ ልጅነት ተመልሶ አይመጣም ተባልኩ እንጂ እውነቱን ለመናገር የዚያ አይነቱ የኑሮ ሁኔታ በጣም ይስማማኝ ነበር፡፡
የኃላፊነትን ቀንበር ሌሎች በተሸከሙልኝ በዚያን ጊዜ፥ እኔ አሳቤን የማውለው ሌላ ነገር ላይ ነበር፡፡ በመመራመርና በመፈላሰፍ፣ ለነገሮች የነበረኝን አመለካከት ትርጉም እሰጠው ነበር፡፡ የዚህ የልጅነት ጊዜዬ የምርምር ውጤት የሆኑትን አንዳንድ አስተሳሰቦች ለምሳሌ ይህል ላካፍላችሁ፥
ሰማይ ማለት - የእኛን አገርና ቀሪውን አለም የሚለይ ድንበር ይመሰለኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም “ፈረንጅ አገር በሰማይ ነው የሚኬደው።” ሲባል ሰምቻለሁ፡፡
ዝናብ ማለት - ሩቅ አገር ያሉ ሰዎች የሚያፈሱት ውሃ፡፡
ፀሐይ ማለት - እግዚአብሔር ወዲያ ሆኖ እኛን ለማየት የሚጠቀምበት ትልቅ ባትሪ - (ያኔ ባትሪ መያዝ የሚችል ትልቅ የሆነ ሰው ብቻ ስለሚመስለኝ ነው።)
ጨረቃ ማለት - በጨለማ ከላይ ቤት ወደታች ቤት ስሮጥ አብራኝ የምትሮጥ ጓደኛ፡፡
ደመና ማለት - ሁልጊዜ ፀሐይ ለመሞቅ ስፈልግ እየመጣ የሚጋርደኝ በሰማይ የሚሄድ ክፉ ነገር፡፡
ከእኛ ቤት በላይ የሚፈሰው ቦይ ሰሜንና ደቡብ የሚለያዩበት ቦታ (ምክንያቱም ቦዩን ተሻግሪ ስሄድ ወደ ሰሜን ሄድኩ ብዬ አስብ ነበር።)
የእኛ ቤት ደግሞ የምድር መሐል ይመስለኝ ነበር። (ወደዚያ ምስራቅ ከሆነ፣ ወደዚህ ምዕራብ፣ ሰሜንና ደቡብ ደግሞ ወደ ላይና ወደ ታች።) ለሌሎችም ብዙ ነገሮች ከእነኚሁ ጋር የሚቀራረቡ ብዙ የራሴ ትርጉሞች ነበሩኝ፡፡ ያኔ ታዲያ ልጅ ነበርኩ፡፡
ትንሽ ከፍ ስል ግን ነገሮች መለወጥ ጀመሩ። “አዋቂ የሚለውን ስማ” እባል ጀመር፡፡ በዕድሜ ከእኔ የበለጡ ሁሉ ደግሞ አዋቂዎች ስለነበሩ እነርሱን ማድመጥ ጀመርኩ፡፡
የማደምጣቸው ሁሉ ደግሞ ብዙ ነገሮች ይነግሩኝ ጀመር፡፡ በተለይም መሠረታዊ ዕውቀት ስለሚባሉ ነገሮች። ሁሉም የየግል አስተያየታቸውን እንደመለኮታዊ እውነት አሳምነው ያቀርቡልኛል፡፡ ስለሕይወት፣ ስለኑሮ፣ ከየት እንደመጣን፣ ለምን እንደምንኖር፣ ወዴት እንደምንሄድ፣ ሁሉም እውነተኛ ነው የሚሉትን የተለያየ አስተሳሰብ ይነግሩኛል፡፡ አሳቡ ሲምታታብኝና ሰጠይቅ፥ “ታላቅህን ማድመጥ እንጂ መጠየቅ ደግ አይደለም!” ሲሉኝ፣ ወይም (እንደ አያቴ) “አይ የዛሬ ልጆች መቼም መቅሰፈታችሁን በራሳችሁ ነው የምታመጡት!” እያሉ ሰውንም እግዚአብሔርንም እንደበደልኩ አድርገው ስለሚያሳቅሉኝ፣ ወይ በፍርሃት አለዚያም “እነርሱ ሊሳሳቱ አይችሉም።” በሚል ግምት ያሉኝን እቀበል ነበር፡፡
ግን ሁልጊዜ ልጅ ሆኖ መኖር የለምና እያደግሁ ስሄድ ወኔዬም እየደፈረ፣ ሰውነቴም እየጐረመሰ፣ አስተሳሰቤም እየተለወጠ መጣ፡፡ ያሉኝን መቀበል ብቻ ሳይሆን መጠየቅን አዘወትር ጀመር፡፡ የማገኘውም መልስ ካላረካኝ ደግሜ መጠየቅ ቀጠልኩ፡፡ እየቆየሁ ስሄድ እነዚያ ለእውቀታቸው መጠን የሌለ መስለው ይታዩኝ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ከነገሩኝ ውስጥ አንዳንዱ የተሳሳተ እንደሆነና እነርሱ ሊነግሩኝ ያልቻሉት ሌላ እውነት መኖሩን ተረዳሁ፡፡
ለምሳሌ፥ ስለመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ተነግሮኝ ነበር፡፡ አንዳንድ ሰዎች ይህ መጽሐፍ በጣም የተከበረ መጽሐፍ ስለሆነ፣ ከተቀመጠበት ማህደር ውስጥ መውጣት የማይገባው፣ ሲያቃዥና ሲያባንን ከራስጌ ቢያስቀምጡት ብቻ የሚረዳ፣ በተለይ ልጆች ከመሳምና ከመሳለም አልፈው ሊዳፈሩት የማይገባ መጽሐፍ መሆኑን ነበር የነገሩኝ፡፡ ሌሎች ደግሞ መጽሐፉ የዱሮ ሰዎች ታሪክ መሆኑን፣ ብዙዎች ዕወነትነቱን የሚጠራጠሩት የያዘውም አሮጌ አሳብ በአሁኑ በሠለጠነው ዘመን ካለው አስተሳሰብ ጋር የማይገጣጠም እንደሆነ ነበር የነገሩኝ፡፡
ነገር ግን ይህ አሮጌ መጽሐፍ የያዘው አሳብ በዘመናዊ የአርኪዎሎጂ ጥናት ዕውነትነቱ ተደጋግሞ የተመሠከረ መሆኑን የነገረኝ አልነበረም፡፡ በተለይም በ1947 ዓ.ም. የተገኙት “የሙት ባህር ጥቅሎች” “Dead Sea Scrolls” የተባሉት ጹሑፎች ብዙ ዘመናዊ ችግሮችን ለመፍቻ ቁልፍ እንደሆኑ ያሰረዳኝ ሰው አልነበረም፡፡ በአጭሩ፣ ይህ መጽሐፍ ዕድሜና ዘመን የማይሽረው፤ መሻሻልና መሠልጠን የማይለውጠው ዘለአለማዊ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን የነገረኝ ማንም አልነበረም፡፡ ይህንን እውነት ቶሎ አለመነገሬ ይቆጨኛል፡፡
ስለኢየሱስ ክርስቶስም ብዙ ነገሮች ተነግረውኝ ነበር፡፡ በዚች ዓለም ላይ ከተመላለሱት ታላላቅ ሰዎች አንዱ እንደነበረ፣ ተወዳዳሪ የሌለው መምህር፣ በቀላሉ ተከታዮችን ማፍራት የቻለ መሪ፣ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን በእስራኤል ምድር ውስጥ የኖረ፣ በወገኖቹ በአይሁዶች ተጠልቶ የተገደለና፣ በዘመኑ የነበሩ አንዳንድ ድሆችና ጐስቋሎች ብቻ ከግዞት የማያወጣን መሢህ ወይም ሥጋ የለበሰ አምላክ ብለው የተከሉት ሰው እንደነበር ተነግሮኛል፡፡
ገና ከመወለዱ ከብዙ ዘመናት በፊት ልደቱን ሕይወቱንና ሞቱን መቃብሩንና ትንሳኤውን የሚያመለክቱ ጥርት ያሉ ብዙ ትንቢቶች የተነገሩለት መሆኑን፣ በሕይወቱም በዚህ አለም በተመላለሰ ጊዜ ከሦስት መቶ በላይ የሆኑ ትንቢቶችን መፈጸሙን የነገረኝ ግን ማንም አልነበረም፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ከዘመናት በፊት ሲጠበቅ የነበረውና በዘመናት ሁሉ ለዘለአለም የሚኖረው፣ ይህ ታላቅ ኀዋ የተመሠረተበት፣ የዚች አለም ታሪክ ሁሉ ያተኮረበት፣ ዕውቀት በሙሉ የፈለቀበት ዘለአለማዊ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የነገረኝ አልነበረም፡፡ ይህንን ዕውነት በተለይ ቶሎ አለማወቄ በጣም ይቆጨኛል፡፡
ስለሰው ተፈጥሮም የተነገሩኝ ብዙ ነገሮች ነበሩ፡፡ ሰዎች ሁለት አይነት እንደሆኑ፣ ጥሩ ወይም መጥፎ፤ ክፉ ወይ ደግ ብቻ ሊሆኑ እንደሚችሉና ደጐችን ወይም ጥሩዎችን እግዚአብሔር እንደሚወዳቸውና እንደሚቀበላቸው፤ ክፉዎችን ወይም መጥፎዎችን እግዚአብሔር ስለሚጠላቸው እንደማይቀበላቸው ነበር የተነገረኝ፡፡ እግዚአብሔር ወዶ እንዲቀበለኝ ጥሩ ለመምሰል አደርግ የነበረው ጥረት አይረሳኝም፡፡
ያልተነገረኝ ነገር ግን ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ መሆኑ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋል … ” ማለቱን የጠቀሰለኝ ሰው አልነበረም፡፡ ሌላው የሚቆጨኝ ደግሞ፥ የኔ ክፋትና የኔ ኃጢአት ምንም ቢበዛ እግዚአብሔር ለእኔ ያለውን ፍቅር ጨርሶ እንደማይቀንሰው የነገረኝ አልበረም፡፡ ይቆጨኛል! ይህንን ከፍቅር የመነጨ ፀጋ ሳላውቅ ጽድቅ ለማግኘት ስል ያደረኳቸውን ነገሮች ሁሉ ሳስብ ይቆጨኛል። ይህንን ዕውነት ያወቅሁ ዕለት አቤት የተሰማኝ ደስታ … ዝማሬ በውስጤ ገባ፡፡ ልቤም በኃይል መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ፍቅር ስለያዘው፡፡
ሌላው የተነገረኝ ደግሞ ደስታና ሰላምን ለማግኘት ቁልፉ ታታሪና ጐበዝ መሆን እንደነበረብኝ ነበር። የተሟላ ኑሮ ለመኖር መጣጣር እንዳለብኝ ነበር። ያንን ካደረግሁ ደስታና ሰላም እንደማይጎለኝ ነበር የተነገረኝ፡፡ ምክንያቱም እንደነርሱ አባባል፥ ገንዘብ ሊገዛው የማይችለው ነገር የለም፡፡ አባቶች “ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ።” ሲሉ ስለ አውሮፕላን አልነበረም የሚያወሩት። ያልተነገረኝ ነገር ግን፥ የሚቆጥሩት አያሌ ገንዘብ ያላቸው፣ ዝናና ክብር የተከተላቸው ብዙዎች ሰላም አጣን በማለት ራሳቸውን እስከማጥፋት መድረሳቸው ነበር፡፡
ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ባዶነት ሲሰማ፣ ስለማወራው ጭንቀት፣ መነሻው ባልታወቀ ሁኔታ ሰላም ማጣት ሲያቅበጠብጥ ገንዘብ እንዴት አቅም እንደሚያንሰው የጠቆመኝ አልነበረም፡፡
እርግጥ አንዳንድ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል፡፡ እንዲህ አይነቱ ሁኔታ በሚያጋጥመኝ ጊዜ የተባለኩት፥
“ትንሽ ብትጠጣ ያዝናናህል … ትንሽ ብታጨስ ከፍ ያደርግሃል … ትንሽ ብትጨፍር ከችግርህ ያወጣሃል።” ነበር ያሉኝ። ከመጠጡ በኋላ ስለሚመጣው ራስ ምታት፣ የጭሱ ኃይል ሲቀንስ ስለሚሰፍርብኝ ድብርት … ከጭፈራው ማግስት በጭንቅላቴ ውስጥ ስለሚፈጠራው ትርምስ ያስጠነቀቀኝ ግን አልነበረም፡፡
ለምን እንዲህ ይሆናል ብዬ እንደገና በጠየኩ ጊዜ “ተወንና!” ተባልኩ፡፡ ለራሴ አላፊው ራሴ ብቻ እንደሆንኩ፣ ከችግሬና ከጭንቀቴ ለመላቀቅም የምችለው በራሴ ጥበብና ጥረት ብቻ እንደሆነ ነው የተነገረኝ፡፡ ታዲያ ትንሹ ችግሬ ሲያፍገመግመኝ፣ ተለቅ ያለው ደግሞ ተስፋ ሲያስቆርጠኝ “አይዞህ” ባይ እንዳለኝ የነገረኝ ማንም አልነበረም፡፡ ክርስቶስ “እኔ ሰላም እንዲሆንላችሁ ሰላምም እንዲበዛላችሁ መጣሁ” ብሎ የሰጠውን የተሰፋ ብርሃን እንዳይ ወይም በሌላ ቦታ፥ “የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእኔ ላይ ጣሉት።” ብሎ ያስተማረው ለእኔም መሆኑን ማን ነገረኝ? ይህንን ሳላውቅ ያሳለፍኩትን ችግርና ብሶት ሳስብ - ይቆጨኛል!
ከዚህ ሁሉ ለመገላገል ብሞትስ ብዬ ጠየኩ … አንዳንዶቹ ከምትክማ ያንተ ነገር አበቃ። ተቀብርህ ምስጥ ማፍራት ብቻ ነው፥ አለቀ … ደቀቀ … በቃ … አከተመ፡፡ ሌሎቹ ግን ሻል ያለ አመለካከት ሰጡኝ፡፡ ከሞትክ በኋላ ሕይወት አለ አሉኝ፡፡ ያለው ቦታ ግን ሁለት ብቻ ነው፡፡ አንዱ ጻድቃን ብቻ የሚገቡበት መንግሥተ ሰማይ ሲሆን ሌላው ደግሞ ለኃጢአተኞች የተዘጋጀው ገሃነመ እሳት ነው አሉኝ፡፡
አዕምሮው በትክክል የሚሠራ ሰው ሁሉ እንዲህ አይነት ምርጫ ሲቀርብለት ቶሎ የሚጠይቀው “ታዲያ እንዴት ሆኜ፣ ምን ሠርቼ ነው መንግሥተ ሰማይ መግባት የምችለው? እኔም ያንን ጥያቄ ጠየኩ።
መንግሥተ ሰማይ ለመግባት ጥሩ ሰው መሆን ብቻ እንደሚገባኝ ጻድቅ ለመሆን በመጣጣር፣ በመጾም፣ በመጸለይ፣ የተራበን በማብላት፣ የታረዙን በማልበስ፣ የታመመን በመጠየቅ ዘና ብዬ መግባት እንደምችል ተነገረኝ፡፡
ነገር ግን ምንም ያህል ጥሩ ብሆን፣ በራሴ ልፋትና ድካም መንግሥተ ሰማይ ሊያስገባኝ የሚችል ጽድቅ ሊኖረኝ እንደማይቻል የነገረኝ አልነበረም፡፡ እንዲውም እኔ ጽድቅ ብዬ የምሠራው ሥራ ሁሉ ከእግዚአብሔር ቅድስና ጋር ሲወዳደር በጣም የቆሸሸ መሆኑን ማንም አልነገረኝም፡፡ የመፅደቄና የደህንነቴ ነገርም እኔ ከምሠራው ሥራና ከማደርገው ድርጊት ጋር በፍጹም ያልተያያዘ፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ ከፍቅሩ ብዛት የተነሳ በሰጠኝ የነጻ የፀጋ ስጦታ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ግን አልነገሩኝም፡፡
ይህንን ሁሉ እውነት አውቄ ከተቀበልሁ በኋላ ግን የሚቆጨ ነገር ሁሉ ለቀቀኝ፡፡ ልጅነቴም በማለፉ አሁን ግድ የለኝም፡፡ ግን ረጋ ብዬ ሳስበው ደግሞ ልጅነቴ መች አለፈ እላለሁ፡፡ ያኔ ለራሴ ማሰብ በማልችልበት ጊዜ እነርሱ ተጠነቀቁልኝ ዛሬም ቢሆን በምደክምበት የሚያግዘኝ፣ የማልችለውን የሚያደርግልኝ፤ ዘለአለማዊ አባት ስላልኝ ልጅነቴ እንዳውም ዘለአለማዊ ሆነ፡፡ ልጅነት ተመልሶ አይመጣም ብለው ለሚተርኩልኝ፣ ወይም እንደኒቆዲሞስ “ሰው … ሁለተኛ ወደ እናቱ ማህፀን ገብቶ ሊወለድ ይችላልን?” ለሚሉኝ የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ እኔ ያገኘሁትን መልስ ለእናንተም ይዞላችሁ ይምጣ እላችኋለሁ፡፡

sorce unknown

Post Reply

Return to “Ethio Art and Culture..ኢትዮ ጥበብ ፤ስነ ጽሁፍ ፤”