በረራ ET 409 - የመጨረሻዎቹ ሁለት ደቂቃዎች

Ethiopian airlines related News, Info, Experience , Comment , Anything
User avatar
selam
Leader
Leader
Posts: 175
Joined: 25 Aug 2009 01:59
Contact:

በረራ ET 409 - የመጨረሻዎቹ ሁለት ደቂቃዎች

Unread postby selam » 28 Jan 2010 22:51

በረራ ET 409 - የመጨረሻዎቹ ሁለት ደቂቃዎች
Wednesday, 27 January 2010 09:33
ImageImage Image Image
ፈልጎ የማዳን ጥረቱ ዛሬም ይቀጥላል
(በጋዜጣው ሪፖርተር)

የበረራ ቁጥር ET 409 ለአንድ ሰዓት ያህል በቤይሩት ራፊቅ ሃሪሪ አለም አቀፍ አይሮፕላን ማረፊያ ከቆየ በኋላ፣ 90 ሰዎችን አሳፍሮ ወደ አዲስ አበባ ለማቅናት ሰኞ ከንጋቱ 9፡35 ላይ ተነሳ፡፡
በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ይበር የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 አውሮፕላን ግን ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ከራዳር ዕይታ መጥፋቱን የቤይሩት አውሮፕላን ማረፊያ በረራ ተቆጣጣሪዎች ያሳውቃሉ፡፡

አስቸጋሪ ነበር በተባለው የአየር ሁኔታ ከማረፊያው ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ የበረረው የዚህ አውሮፕላን አሰቃቂ ዕጣ የታወቀው የአይን ምስክሮች ከአካባቢው ሰማይ ከፍተኛ የእሳት ብልጭታ ወደ ሜዲትራኒያን ባህል እየተምዘገዘገ ሲወርድ ማየታቸውን ካሳወቁ በኋላ ነበር፡፡

አንዳንድ ዘገባዎች ኢትዮጵያውያኑ አብራሪዎች የመጀመሪያዎቹን ሁለት ደቂቃዎች ከቤይሩት ማረፊያ ከሚገኘው የአየር መቆጣጠሪያ በተደረገላቸው እገዛ ያበሩ እንደነበር ይገልፃሉ፡፡

የቤይሩት የአየር መንገድ ባለሥልጣናት፣ ዝናብና መብረቅ በቀላቀለ ተመሳሳይ የአየር ሁኔታ ወቅት የሚደረግ የተለመደ አሰራር መሆኑንም ለዜና አውታሮች አሳውቀዋል፡፡

አደጋው ከተከሰተ ጀምሮ እየተደረገ ባለ የፍለጋ ሥራ እስከ ትናንት ማታ 25 አስከሬን የተገኘ ቢሆንም፣ የአካባቢው የአየር ሁኔታ የፍለጋ ሥራውን አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ ከተገኙት ውስጥ 6 ኢትዮጵያውያንና 8 ሊባኖሳውያን መሆናቸውም ታውቋል፡፡

ከፍለጋ ሥራው አዳጋችነት የተነሳ የሊባኖስ መንግሥት የአሜሪካ የባህር ኃይል በፍለጋው ሥራ እገዛ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን የሚመራ የኢትዮጵያ አጣሪ ቡድንን ጨምሮ አንድ የእንግሊዝ የአደጋ ጊዜ ፍለጋ ሥራ ላይ የተሰማራ ብሌክ ኢመርጀንሲ ሰርቪስስ (Blake Emergency Services) የተባለ ድርጅትና የተባበሩት መንግሥታትም እንደሚገኙበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ግርማ ዋቄ ሰኞ እለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቀዋል፡፡

ካፒቴን ደስታ ዘርኡ የአየር መንገዱ በረራ ኦፕሬሽንስ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የአደጋ ጊዜ ምላሽ ማዘዣ ዋና ዳይሬክተር ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት፣ አየር መንገዱ ከእንግሊዙ ድርጅት ጋር ከተወሰነ ጊዜ በፊት ስምምነት መግባቱን እና በአደጋ ጊዜ ምላሽ እና በተለያዩ የፎረንዚክስ እና የዲኤንኤ ምርመራዎች ላይ የካበተ ልምድ እንዳለው አሳውቀዋል፡፡

ከዚሁ ድርጅት እና ከኢትዮጵያ ሰኞ እለት ከበረሩት ቡድኖች በተጨማሪ፣ በትናንትናው እለት በርካታ አባላት ያሉት ቡድን ከብሌክ ኢመርጀንሲ ሰርቪስስ እና ከኢትዮጵያ፣ የተለያዩ የሕክምና እና የምርመራ መሣሪያዎችን ይዞ ወደ ቤይሩት አቅንቷዋል፡፡

የሊባኖስ የአየር ጥቆማ መስሪያ ቤትና የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣኑ፣ ከፍተኛ ማዕበል፣ እስከ 18 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሚደርስ ቅዝቃዜ እንዲሁም ድቅድቅ ጭጋግ ቀጣይ የፍለጋ ሥራውን አስቸጋሪ ያደርጋል ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡

እስካሁን በፍለጋው የተገኙ አስከሬኖችን ማንነት ለማጣራት የዲ.ኤን.ኤ (DNA) ምርመራ እየተካሄደ መሆኑም ተገልጿል፡፡

51 ሊባኖሳውያን፣ 23 ኢትዮጵያውያን፣ አንድ እንግሊዛዊ፣ አንዲት ፈረንሳዊት፣ አንድ ሶሪያዊ፣ አንድ ቱርካዊ እና አንድ ኢራቃዊ ተሳፋሪዎች፤ እንዲሁም ከሁለቱ አብራሪዎች ጋር አምስት የበረራ አስተናጋጆችን እና አንድ ኢትዮጵያዊ የበረራ ደህንነት አባልን ይዞ መጓዝ የጀመረው ቦይንግ አውሮፕላን ላይ ለደረሰው አደጋ መንስኤው ገና በውል አልታወቀም ብለዋል አቶ ግርማ ዋቄ፡፡

አደጋው መድረሱን ተከትሎ ይሰጥ የነበረው ግምት፣ ምናልባት አውሮፕላኑ በመብረቅ ተመትቶ ይሆናል የሚል ቢሆንም፣ አቶ ግርማን ጨምሮ ስለአቪዬሽን ዕውቀት ያላቸው ግን ማጣራቱ ሳይጠናቀቅ በፊት እርግጠኛ መሆን አይቻልም ይላሉ፡፡

አንዳንድ ከአየር በረራ ሥራ ጋር ግንኙነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን አስተያየት ሰጪዎች የአይን ምስክሮቹ እንዳሉት "አውሮፕላኑ በአየር ላይ ፍንዳታ ደርሶበት ከሆነ በመብረቅ የመመታቱ ነገር አጠራጣሪ ይሆናል" ብለዋል፡፡

አውሮፕላኑ በሜዲትራኒያን ከተከሰከሰ ከሰዓታት በኋላ ከባሕሩ ዳርቻ የአውሮፕላኑ ስብርባሪና በውስጡ የነበሩ የሕጻናት አሻንጉሊቶች፣ ሻንጣዎች እና የመድሃኒት ብልቃጦችን የመሳሰሉ ቁሳቁሶች ተገኝተዋል፡፡

በበረራ ቁጥር ET 409 ውስጥ ተሳፍረው ከነበሩት ውስጥ የ3 ዓመትና የ4 ዓመት ሊባኖሳውያን ህፃናት ይገኙበት እንደነበር ይፋ የተደረገ የተሣፋሪዎች ስም ዝርዝር ያሳያል፡፡

አደጋው ከመድረሱ በፊት ስለነበረው ሁኔታ የተለያዩ ምስክሮችና አስተያየቶች እየተሰጡ ሲሆን፣ አንዳንድ ዘገባዎች የሊባኖስን የጦር ኃይል ዋቢ በማድረግ አውሮፕላኑ አኮብኩቦ ከተነሳ በኋላ በእሳት መያያዙን ይጠቁማሉ፡፡

ሌሎች ደግሞ እስከ ጭራሹ የአይን ምስክሮቹ አየነው ያሉት ከፍተኛ የእሳት ብልጭታ ጭምር እንደሚያጠራጥራቸው ይናገራሉ፡፡

"በአውሮፕላን አደጋ ወቅት የአይን ምስክር ነን የሚሉ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ፍንዳታ ስለመስማታቸው ወይም ኃይለኛ ወላፈን ስለማየታቸው ይመሰክራሉ" ሲል በአሜሪካ የሚገኘው የበረራ ደህንነት ፋውንዴሽን ጥርጣሬውን ገልጿል፡፡

በተፃራራዊው፣ አንዳንድ የዜና አውታሮች፣ ከቤይሩት አውሮፕላን ማረፊያ የደህንነት ካሜራዎች የተገኘ ባሉት ፊልም አንድ አውሮፕላን በጨለማ ሲበርና ከፍተኛ የሆነ የብርሃን ብልጭታ ሲታይ በድረ ገፃቸው አቅርበዋል፡፡ የቦይንግ 737 አውሮፕላኑን መከስከስ ተከትሎ የሊባኖስ ባለስልጣናትም መግለጫዎችን እየሰጡ ይገኛል፡፡

የአገሪቱ የትራንስፖርት ሚኒስትር ለአሶሽየትድ ፕሬስ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያዊው አብራሪ ከመቆጣጠሪያ ማማው ይሰጠው የነበረውን የአቅጣጫ አመላካች መልዕክት በተፃረረ መልኩ ሌላ መስመር ይዞ መጓዙን ገልፀዋል፡፡

"ከመቆጣጠሪያ ማማው አቅጣጫውን እንዲያስተካክል መመሪያ ቢሰጠውም በጣም ፈጣንና ያልተለመደ አጠማዘዝ በማድረግ ከራዳር ዕይታ ጠፋ" ብለዋል ጋዚ አሪዲ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የሊባኖስ ባለስልጣናት አውሮፕላኑ የሽብር ጥቃት ሰለባ እንዳልነበረ ይገልፃሉ፡፡

"ሆን ተብሎ የተፈፀመ ወይም የሰዎች እጅ አለበት ብለን አናምንም" ሲሉ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሚቼል ሱሌይማን ተናግረዋል፡፡

አደጋው የደረሰበት ቦይንግ 737 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኪራይ ይጠቀምበት የነበረ ሲሆን አምራቹ ኩባንያ የራሱን መርማሪዎች የአደጋውን መንስኤ እንዲያጣሩ ወደ ሊባኖስ ልኳል፡፡

ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተሰነዘሩ ያሉትን ግምታዊ አስተያየቶች አስመልክቶ ካፒቴን ደስታ ለሪፖርተር እንደገለፁት "በአሁኑ ወቅት ግምታዊ አስተያየት ተገቢ አይደለም፡፡ ምርመራው ሳይጠናቀቅ አስተያየት መስጠት ከሙያዊ ስነምግባር ውጪ ነው፡፡"

አክለውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት ትኩረት የሚሰጠው የተሣፋሪዎችን ቤተሰቦች መንከባከብ፣ መረጃ በጊዜ እንዲያገኙ ማድረግና የሟቾችን አስከሬን በማፈላለግ የተረፉ ካሉም እነሱን ማዳን ላይ ነው ብለዋል፡፡

ሰኞ እለት ማታ ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት 10 የተሳፋሪ ቤተሰቦችን አየር መንገዱ ሙሉ ወጪ ሸፍኖ ወደ ቤይሩት እንደላካቸው ካፒቴን ደስታ ገልፀው፣ በትላንትናው ምሽት ደግሞ በአየር መንገዱ ወደ ቤይሩት መሄድ እንደሚፈልጉ ተጠይቀው ምላሽ የሰጡ በበረራው የነበሩ የአየር መንገዱ ሰራተኞች ቤተሰቦች ሄደዋል፡፡

በተጨማሪም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥዩም መስፍን፣ የትራንስፖርት እና የመገናኛ ሚኒስቴሩ አቶ ዲሪባ ኩማ እና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ዳይሬክተር አቶ ወሰንየለህ ሁነኛው የሚመራ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ወደ ቤሩት አቅንቷል፡፡

የፍለጋ ሥራው ዛሬ ሙሉ ቀን እንደሚቀጥልም ካፒቴን ደስታ ለሪፖርተር አሳውቀዋል፡፡ ወደ ሕትመት እስከገባንበት ሰዓት ድረስ የበረራው መረጃ ሳጥን (Black Box) እና ድምፅ መቅረጫው እንዳልተገኘም አክለው ገልፀዋል፡፡

ከቤይሩት ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት 23 ኢትዮጵያውያን ተሣፋሪዎች በሙሉ ሴቶች ነበሩ፡፡
Last edited by selam on 28 Jan 2010 23:04, edited 2 times in total.

User avatar
selam
Leader
Leader
Posts: 175
Joined: 25 Aug 2009 01:59
Contact:

Re: በረራ ET 409 - የመጨረሻዎቹ ሁለት ደቂቃዎች

Unread postby selam » 28 Jan 2010 22:55

ካፒቴኑ
Wednesday, 27 January 2010 09:26
አደጋው የደረሰበትን ቦይንግ 737 - 800 አብራሪ የነበሩት ካፒቴን ሀብታሙ በንቲ ተወልደው ያደጉት በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ ዞን በነቀምት ከተማ ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በ1974 ዓ.ም. ካጠናቀቁ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና አጥጋቢ ውጤት በማምጣት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1975 ዓ.ም. ገብተዋል፡፡ በ1979 ዓ.ም. በኬሚስትሪ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዳገኙ፣ በታላቅ ወንድማቸው አበረታችነት በ1979 ዓ.ም. አድማስ ኤር ሰርቪስ (የፀረ አረም መርጫ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት) በተለማማጅ አብራሪነት እንደገቡ የቅርብ ጓደኞቻቸው ገልፀውልናል፡፡ ዕድሜያቸው በአርባዎቹ መጀመሪያ እንደሆነም አክለው ገልፀዋል፡፡ ከሁለት ዓመት ስልጠና በኋላ ከ1981 ዓ.ም. ጀምሮ በአድማስ ኤር ሰርቪስ ውስጥ በአበራሪነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ በመቀጠልም ወደ ኢትዮጵያ አየርመንገድ በመግባት ተከታታይ ስልጠናዎችን በመውሰድ በፎከር እና ቦይንግ አውሮፕላኖች ላይ በረዳት እና በዋና አብራሪነት ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ በረራዎች ወደ ስምንት ሺህ ያህል ሰዓት ያጠራቀሙት ካፒቴን ሃብታሙ ባለፉት ቅርብ ዓመታት በአብዛኛው ያበረሩት ቦይንግ 737 አውሮፕላን ሲሆን ይህም አውሮፕላን በአብዛኛው አገልግሎት የሚሰጠው በአፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ አገሮች ውስጥ ነው፡፡

ካፒቴን ሃብታሙ ትዳር አልመሰረቱም፡፡ በቦይንግ 737 ላይ ዋና አብራሪ የሆኑትም በቅርቡ ነው፡፡ ቀደም ሲል በፎከር አውሮፕላን ላይ በዋና አብራሪነት ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በአየር መንገዱ አሰራር መሰረት ብዙውን ጊዜ በፎከር ላይ በረዳት አብራሪነት ይሰሩ እና ከዚያ ወደ ቦይንግ አውሮፕላኖች ተሻግረው እንደገና በረዳት አብራሪነት ያገለግላሉ፡፡ በመቀጠልም ወደ ፎከር ተዛውረው ካፒቴን (ዋና አብራሪ) ሆነው ይሰራሉ፡፡ እያንዳንዱ ሽግግር የራሱ የሆነ ትምህርትና ፈተና አለው፡፡ በመጨረሻም በፎከር ላይ በካፒቴንነት ለተወሰኑ ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ወደ ቦይንግ ካፒቴንነት ያድጋሉ፡፡ በአጠቃላይ አንድ ካፒቴን ለማፍራት ከ10 እስከ 13 ዓመት ይፈጃል፡፡

ካፒቴን ሃብታሙ ቅዳሜ ማታ ቦይንግ 737-700 አውሮፕላን በማብረር ወደ ቤይሩት የተጓዙ ሲሆን፣ ይህንኑ አውሮፕላን ለሌሎች ተመላሽ ፓይለቶች አስረክበው ቅዳሜ ሌሊቱን በቤይሩት እረፍት አድርገዋል፡፡ አደጋው የደረሰው ከረዳት አብራሪያቸው አሉላ ታምራት ጋር የመልስ ጉዞ ለማድረግ በተነሱበት ሰዓት ነበር፡፡ አየር መንገዱ ካፒቴን ሃብታሙን አየር መንገዱን ከ20 ዓመት በላይ ያገለገሉ ብቃት ያላቸው ፓይለት ሲል አሞግሷቸዋል፡፡

User avatar
selam
Leader
Leader
Posts: 175
Joined: 25 Aug 2009 01:59
Contact:

Re: በረራ ET 409 - የመጨረሻዎቹ ሁለት ደቂቃዎች

Unread postby selam » 28 Jan 2010 22:59

አውሮፕላኑ
Wednesday, 27 January 2010 09:23

ቢ737 አውሮፕላን የቦይንግ ካምፓኒ የሚመካበት አውሮፕላን ነው፡፡ በገበያ ላይ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው የሚነገርለት ይህ አውሮፕላን በከፍተኛ ሽያጭ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ቀዳሚ ሥፍራ የያዘ ነው፡፡ ይህ አውሮፕላን መመረት ከጀመረ እ.ኤ.አ ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ 6000 ቢ737 አውሮፕላኖች ተሽጠዋል፡፡ በ43 ዓመት የአገልግሎት ታሪኩ ውስጥ አደጋ የደረሰባቸው የቢ737 አውሮፕላኖች ብዛት 68 ነው፡፡ አውሮፕላኖቹ ከበረሩበት ሰዓት ብዛት አኳያ 68 አደጋ ብዙ የሚባል እንዳልሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በግዥ አምጥቶ የሚጠቀምባቸው አምስት ቢ737-700 አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን በኪራይ ..ሲ አይቲ ኤሮስፔስ.. ከሚባል ኩባንያ የመጣው ቢ737-800 አውሮፕላን የተመረተው እ.ኤ.አ በ2002 ዓ.ም. ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኑን የተከራየው ባለፈው መስከረም ወር ሲሆን ቀደም ሲል የኦማን አየር መንገድ አውሮፕላኑን ለአንድ ዓመት በኪራይ ተጠቅሞበታል፡፡ በአጠቃላይ የቢ737 አውሮፕላን የበረራ ደህንነት ጥሩ እንደሆነ የሚናገሩት የአቪዬሽን ባለሙያዎች በአንድ ወቅት አውሮፕላኑ ከራዳር ጋር የተገናኘ ችግር እንደነበረበት እና ይህንንም ቦይንግ ማስተካከሉን ገልፀዋል፡፡

የደረሰውን አደጋ በማስመልከት ለአገር ውስጥ እና ለውጪ ጋዜጠኞች ከትናንት በስቲያ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ግርማ ዋቄ አይሮፕላኑ ምንም ዓይነት የቴክኒክ ችግር እንዳልነበረበት ገልፀዋል፡፡ አይሮፕላኑ እሁድ ማምሻውን ወደ ቤይሩት ያለምንም ችግር መጓዙን የገለጹት አቶ ግርማ የቴክኒክ ፍተሻ በዚሁ አውሮፕላን ላይ ታህሳስ 16 ቀን 2002 ዓ.ም. እንደተካሄደ እና ምንም አይነት እንከን እንዳልተገኘበት ገልፀዋል፡፡ ቢ737 አውሮፕላን በአዲስነቱ 76 ሚሊዮን ዶላር ያወጣል፡፡

በቢ 737-800 አውሮፕላን ላይ በቅርቡ የደረሱ አደጋዎች በቱርክ አየር መንገድ እና በኬንያ ኤርዌይስ ላይ ነው፡፡ በየካቲት 2001 ዓ.ም. ንብረትነቱ የቱርክ አየር መንገድ የሆነ 737-800 አውሮፕላን አምስተርዳም ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ለማረፍ ሲቃረብ እርሻ ውስጥ ወድቆ የዘጠኝ ሰዎች (ተሳፋሪና የአውሮፕላን ሰራተኞች) ህይወት አልፏል፡፡

አሁን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ከደረሰው አደጋ ጋር የሚመሳሰለው በሚያዚያ 1999 ዓ.ም. በኬንያ ኤርዌይስ ላይ የደረሰው አደጋ ነው፡፡ ንብረትነቱ የዚሁ አየር መንገድ የሆነ ቢ737-800 አውሮፕላን ከዱዋላ ካሜሩን ተነስቶ ወደ ናይሮቢ ለማምራት፣ ከዱላዋ አየር ማረፊያ ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ጥቅጥቅ ባለ ደን ውስጥ ተከስክሶ በውስጥ የነበሩ 117 መንገደኞች እና የአውሮፕላኑ ሠራተኞች በሙሉ ህይወታቸው አልፏል፡፡ አደጋው በደረሰበት ወቅት ልክ እንደአሁኑ እንደ ቤይሩቱ በዱዋላም መጥፎ የአየር ጠባይ ነበር፡፡ በወቅቱ ሃይለኛ ነጎድጓድ የቀላቀለ ዝናብ በመጣል ላይ ነበር፡፡ የአቪዬሽን ባለሙያዎች እንደሚናገሩት የቢ737 አውሮፕላን በበረራ ደህንነት ረገድ መልካም ስም እንዳለው ነው፡፡

User avatar
selam
Leader
Leader
Posts: 175
Joined: 25 Aug 2009 01:59
Contact:

Re: በረራ ET 409 - የመጨረሻዎቹ ሁለት ደቂቃዎች

Unread postby selam » 28 Jan 2010 23:07

የኢትዮጵያውያኑ የመንገደኞች ስም ዝርዝር
Wednesday, 27 January 2010 09:18

1. አዲስ አበራ ደምሴ
2. ባህርነሽ መገርሳ
3. ቅድስት ወልደማርያም
4. ኤልሳቤጥ ጥላሁን ሀብተማርያም
5. ራሄል ታደሰ
6. እቴነሽ አድማሴ
7. ወይንሸት መንግሥቱ መላኩ
8. አዜብ በትረ ከበደ
9. ትዕግስት ሽኩር
10. ሀኒ ገብሬ ገምበዞ
11. አሉነሽ ተክሌ
12. ሽቱ ኑሪ
13. ሰላም ዘግዳያ
14. ይክማ መሀመድ
15. ሰብለ አግዜ
16. አይናለም ተሰማ
17. እየሩስ አለም ታደሰ
18. መኪያ ስሩር
19. ላቀች ዘለቀ
20. ትዕግስት አኑራ
21. አስካለች ሰቦቃ
22. መሰሉ በሻህ
ምንጭ - ዴይሊ ስታር (ሊባኖስ)
..ማ 409 የበረራ ሰራተኞች ስም ለማግኘት አየር መንገዱን ጠይቀን ካፒቴን ደስታ ዘርኡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ኦፕሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት እና የአደጋ ጊዜ ምላሽ ማዘዣ ዋና ዳይሬክተር ..የፈልጎ ማዳን ሥራው ሳይጠናቀቅ የሰራተኞቹን ስም ይፋ አናደርግም.. ብለዋል፡፡
ሆኖም የሪፖርተር ጋዜጣ ከተለያዩ ምንጮች የበረራ ሰራተኞችን ስም ለማግኘት ችሏል፡፡

የአውሮፕላኑ የበረራ ሠራተኞች
አብራሪዎች

1. ሐብታሙ በንቲ (ዋና አብራሪ)
2. አሉላ ታምራት (ረዳት አብራሪ)

የበረራ አስተናጋጆች

1. ሰብለወንጌል ስዩም
2. ገሊላ ጌዲዮን
3. ሰብለ ገ/ፃዲቅ
4. ሕሊና አዲስ
5. ነፃነት ይፍሩ

የበረራ ደህንነት

1. ስሙ የማይጠቀስ

User avatar
selam
Leader
Leader
Posts: 175
Joined: 25 Aug 2009 01:59
Contact:

Re: በረራ ET 409 - የመጨረሻዎቹ ሁለት ደቂቃዎች

Unread postby selam » 28 Jan 2010 23:16

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ደህንነት ሪከርድ
Wednesday, 27 January 2010 09:11
[justify](በጋዜጣው ሪፖርተር)

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተቋቋመው በታኅሣሥ ወር 1937 ዓ.ም. ሲሆን፣ የመጀመሪያውን በረራ ያደረገው በ1938 ዓ.ም. ወደ ካይሮ ነበር፡፡ ይህ በረራ ከተከናወነ እነሆ 64 ዓመት ሆኖታል፡፡ ዛሬ አየር መንገዱ 35 የአፍሪካ ከተሞችን ጨምሮ በመላው ዓለም 56 መዳረሻዎች አሉት፡፡

በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጐልቶ የሚነገርለት ትልቁ ስኬቱ የበረራ ደህንነት አስተማማኝነቱ ነው፡፡ ከአፍሪካ አየር መንገዶች ሁሉ እጅግ በጣም ተመራጭ የሚያደርገውም የራሱን የበረራ ትምህርት ቤት፣ የጥገና ማዕከልና ሌሎች ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ዘመን ካፈራው ቴክኖሎጂ ጋር መጠቀም መቻሉ ነው፡፡

አንዲ ካርሊንግ የተባሉ ፀሐፊ ከትናንት በስቲያ ባሠፈሩት ጽሑፍ "አፍሪካ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ ጉዞ ያደርጉ ሰዎች ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ልዩ ቦታ ይኖራቸዋል፡፡ አየር መንገዱ ሌሎች የአውሮፓ አየር መንገዶች ሳይቀር የሚቀኑበት የራሱ የሆነ የአገልግሎት ጥራትና የቴክኒክ ድጋፍ አለው፡፡"

ፀሐፊው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ቤይሩት አቅራቢያ መከስከሱን ተከትሎ ባቀረቡት ዘገባ፣ የአየር መንገዱ አብራሪዎች በጥራታቸው ታዋቂ ሊሆኑ የቻሉት ተራራማ በሆኑ የአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ውስጥ እጅግ በጣም አታካች በሆኑ በርካታ በረራዎች በመፈተናቸው ነው፡፡ "ብዙዎቹ እንዲህ ዓይነቶቹን በረራዎች በኢትዮጵያና በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በማድረግ ጥርሳቸውን የነቀሉበት" ነው ሲሉ አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡

አየር መንገዱ ከሚመካባቸው አብራሪዎች በተጨማሪ የቴክኒሸያኖቹ ብቃት ለራሱ ብቻ ሳይሆን፣ ለበርካታ የአፍሪካ እና የሌሎች አየር መንገዶች የተረፈ መሆኑን ፀሐፊው አስታውሰው፣ የቴክኒሺያኖቹ ብቃትም ከአውሮፓውያኑ ጋር ሲነፃፀር ወይ ይበልጣል አልያም ተመጣጣኝ ነው ብለዋል፡፡

"በኢትዮጵያ አየር መንገድ በርካታ በረራዎች አድርጌአለሁ፣ ለኔ ተመራጩ አየር መንገድ ሲሆን፣ የበረራ ደህንነቱም አስተማማኝ ነው" ሲሉ በስሜት ተናግረዋል፡፡

የአቪዬሽን ኤክስፐርቶች አፋቸውን ሞልተው የሚናገሩት በመላው ዓለም በበረራ ደህንነታቸው ከተመሰከረላቸው ምርጥ አየር መንገዶች ጐን በኩራት መቆም የሚችለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሆኑን ነው፡፡ በበረራ ደህንነት ሪከርዱ በአፍሪካ አህጉርም ሆነ በመላው ዓለም መልካም ዝናን የተጐናፀፈ ተመራጭ አየር መንገድ እንደሆነም እየተዘገበ ነው፡፡

በአፍሪካ ውስጥ በሚያደርጋቸው በረራዎች ከሌሎች አየር መንገዶች በበለጠ ገበያውን ለመቆጣጠር የቻለው ከአገልግሎት ጥራቱ በተጨማሪ ለበርካታ መንገደኞች አሳሳቢ የሆነው የበረራ ደህንነትን አስተማማኝነት በአሳማኝ ሁኔታ ስለሚያረጋግጥም ነው፡፡ ለዚህም ነው ሰሞኑን በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚወጡት ዘገባዎች የአየር መንገዱን የበረራ ደህንነት ሪከርድ አጐልተው የሚያሳዩት፡፡

የቤይሩቱ አደጋ መንስኤ ለጊዜው በውል ባይታወቅም፣ ካሁን በፊት የደረሱት አደጋዎች በአብራሪዎች፣ በቴክኒሻኖችና እንዲሁም በአጠቃላዩ የአየር መንገድ የሥራ እንቅስቃሴ በተከሰቱ ችላ ባይነቶች ወይም ከደረጃ በታች በሆኑ ምክንያቶች አልነበሩም፡፡ ይልቁንም በሌሎች ውጫዊ ምክንያቶች ሁለት አደጋዎች መከሰታቸው አይዘነጋም፡፡

ከበረራ አስተናጋጆች (ሆስተሶች) ጀምሮ በተለያዩ የሥራ ክፍሎች ውስጥ ተመድበው የሚሠሩት ከ5 ሺህ በላይ ሠራተኞቹ ጭምር ለዚህ የበረራ ደህንነት ሪከርድ መከበር ተሳትፎአቸው ወሳኝ መሆኑን ማንም ይረዳዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ 37 የተለያዩ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን የሚጠቀመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዘመኑ ሥሪት የሆኑትን ቦይንግ 787 ድሪምላይነር ጄቶችን ጨምሮ 35 አውሮፕላኖችን በተጨማሪ ለማስገባት የግዢ ትዕዛዝ ከቦይንግ፣ ከኤርባስና ከቦምባርዲየር ኩባንያዎች ጋር አድርጓል፡፡

እ.ኤ.አ በ2009/10 የበጀት ዓመት 150 ሚሊዮን ዶላር የተጣራ ትርፍ ለማግኘት አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ ያለው አየር መንገዱ፣ ባለፈው ዓመት በርካታ አየር መንገዶች ለኪሣራ ሲዳረጉ ከጥቂት አትራፊ አየር መንገዶች ተርታ በመሰለፉ በአፍሪካ ዝናው ጣራ መንካቱ ይታወሳል፡፡

አየር መንገዱ በኅዳር ወር 2002 ዓ.ም. በአፍሪካ አየር መንገዶች ማኅበር "የዓመቱ አየር መንገድ ሽልማት"፣ በነሐሴ ወር 2001 ዓ.ም. "የ2008 ኮርፖሬት አቺቭመንት አዋርድ"፣ የብራስልስ ኤርፖርት ኩባንያን በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ሽልማት ለተለያዩ ተግባሮቹ ሲያገኝ፣ "የ2008 የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ" የሚለውንም ሽልማት አግኝቷል፡፡ እነዚህ ሽልማቶች አየር መንገዱ በተለይ በአፍሪካ አህጉር አስተማማኝ አየር መንገድ መሆኑን ያመላክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በነዚህ ሁሉ በርካታ ዓመታት የገጠሙት ጉልህ አደጋዎች የቤይሩቱን ጨምሮ ሦስት ብቻ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው እ.ኤ.አ በ1988 ዓ.ም. ከባህር ዳር ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመነሳት ላይ የነበረው አውሮፕላን ሞተር ውስጥ በርካታ ወፎች በመግባታቸው የደረሰው አደጋ ነው፡፡ በዚህ አደጋ ከ104 መንገዶኞችና ከአውሮፕላኑ ሠራተኞች ውስጥ 31 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፡፡

እ.ኤ.አ በ1996 ዓ.ም. ሦስት ጠላፊዎች አውሮፕላኑን አስገድደው ወደ አውስትራሊያ ለመውሰድ በፈጠሩት ትርምስ በደረሰው አደጋ አውሮፕላኑ ኮሞሮስ ደሴት አቅራቢያ ህንድ ወቅያኖስ ላይ በመውደቁ ከ175 መንገደኞችና የአውሮፕላኑ ሠራተኞች መካከል 126 የሚሆኑት መሞታቸው ይታወሳል፡፡ ለጊዜው የቤይሩቱ አደጋ መንስኤ ምን እንደሆነ በይፋ የታወቀ ነገር እስካሁን ባይኖርም፣ ለአደጋው መንስኤ ናቸው የተባሉ አንዳንድ ግምቶች እየወጡ ነው፡፡ ለጊዜው የተለየዩ አገሮች ዜጎች መንገደኞችንና የአውሮፕላኑን ሠራተኞች ጨምሮ የ90 ሰዎች እጣ ፈንታ ባለየበት በዚህ ወቅት ትክክለኛው መረጃ እስከሚገኝ ውጤቱን መጠባበቅ ግድ ይላል፡፡[/justify]


Return to “Ethiopian Airlines”