ኦነግ “የማይበጀን ይገንጠል!” አለ ኢትዮጵያም ደስ አላት! (አቤ ቶኪቻው)

User avatar
zeru
Leader
Leader
Posts: 952
Joined: 19 Aug 2009 17:01
Contact:

ኦነግ “የማይበጀን ይገንጠል!” አለ ኢትዮጵያም ደስ አላት! (አቤ ቶኪቻው)

Unread post by zeru » 03 Jan 2012 17:45

ኦነግ “የማይበጀን ይገንጠል!” አለ ኢትዮጵያም ደስ አላት! (አቤ ቶኪቻው)


አቤ ቶኪቻው
abeto2007@yahoo.com
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ቀረብ ብለው ሲከታተሉ ለቆዩ እና የሀገሪቷ ጉዳይ ግድ ይሰጠናል ለሚሉ “ዋና” የአገር ልጆች ታላቅ የምስራች ተሰምቷል። ይህውም አንጋፋው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ኦነግ በይፋ የመገንጠል ሀሳቡን ትቶ ከሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች ጋር በመሆን “ችርቻሮ” ለሚወደው ገዢው መንግስታችን “በጅምላው ሞክረን!” ሊለው ቆርጦ መነሳቱን ማወጁ ነው።
የኛ ሰፈር ፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ፤ “ኢህአዴግ ጥሎበት ችርቻሮ ይወዳል። ሲገዛ በብሄር እና በጎጥ፤ ገፋ ሲልም በሀይማኖት እየቸረቸረ ነው።” ይሉታል። ታድያ አሁን አሁን ሁሉም ነቄ ሆነና በብሄር ልቸርችርህ ሲሉት “ውይ ውይ… አያዋጣም ከቦታውም እንዲህ አልመጣም” ማለት ሲጀምር ለገዢው ትልቅ የራስ ምታት ነው? ይላሉ።
የምር ግን ወዳጄ… ከቦታው እኮ በችርቻሮ አልመጣንም። አይደል እንዴ? ከዋናው ቦታ ጀምረን እንቋጠር ካልን ኦኮ ሁሉም “የአዳም እና ሄዋን” በሙስሊሙም ቢሆን “የአደምና ሃዋ” ልጅ ነው። ስለዚህ ከቦታው ሲመጣ አንድ ነው። ታድያ አሁን እንከፋፍልህ (ነጠላ ሰረዝ) እንቸርችርህ (ነጠላ ሰረዝ) እንሸንሽንህ ቢሉት፤ ከህገወጥ ግንባታ እና ኮንትሮባንድ ንግድ ተለይቶ እንዴት ይታያል? እናም ትላንት ከኦነግ የተሰማው የአንድነት ጥሪ፤ የችርቻሮ ዘመን ሊያበቃ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለን ደፍረን መናገር እንችላለን?
ብሶት የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት… ሲያውቅ በድፍረት፣ አሁንም ሲያውቅ በግዴለሽነት፣ አሁንም ሲያውቅ እግዜርን ባለመፍራት፣ እንዲሁም አልፎ አልፎ፤ ሳያውቅ በስህተት በርካታ ብሶቶችን በህብረተሰቡ ላይ እየዘራ ነው ይሉታል። “ይሉታል” ነው ያልኩት። እኔማ ምን በወጣኝ አህአዴግን በክፉ አነሳዋለሁ…? አንቀባሮ ካገር ያሰደደኝ አይደለምን? (“ሎል” አሉ የፌስ ቡክ አራዶች ሳቅ በሳቅ ማለት ነው። ቅንፍ ውስጥ ከገባሁ አይቀር… በነገራችን ላይ ብዬ ቀጥላለሁ… በነገራችን ላይ፤ የፌስ ቡክ ወዳጆቼ ከተሰደድኩበት ቀንና ሰዓት አንስቶ እንደምን አላችሁልኝ? እኔ ከእናንተ መረጃ እየወሰድኩ የወሬ ጥሜንም እየቆረጥኩ ነውና… ደህና ነኝ። እባካችሁ የምንናፍቃትን ሀገር ወሬ በ “እንደወረደ” ቋንቋ በወዳጃማች የጨዋታ ስልት ሁልግዜም አውጉን…ደስም ይለናል። እላለሁ።)
እናልዎ ወዳጄ ብሶት የወለደው ኢህአዴግ በሰዉ ላይ ብሶት እየዘራ ብሶቱንም ሲያሳድግና ሰያፋፋ አብዛኛውን የሀገሪቱ ክፍል በብሶት ምርት ራሱን ችሎ “በቂ” የሆነ ብሶተኛ በየግዜው እየተመረተ ይገኛል። (እባካችሁ በየ አራት ነጥቡ “አሉ”ን እያስገባችሁ አንብቡልኝ። ኋላ ኢህአዴግዬ የወሬው ምንጭ እኔ እንዳልመስለውና “የአገርን መረጃ አሳልፎ በመስጠት” ብሎ እንዳይከሰኝ።) ከዚህ ከብሶት ምርት ጋር ተያይዞ፤ አንዳንዶች ምን እንደሚሉ ሰምተውልኛል? “በየግዜው አስመዘገብን የሚባለው አስራ አንድ ነጥብ ምናምን ከመቶ “የብሶት እንጂ የብልጥግና እድገት!” አይደለም።” እያሉ ሲያሸሙሩ ሰምቻለሁ።

የምር ግን ወዳጄ ሀገራችን በግብርና ምርት ከፍ ማድረግ ሲገባን በብሶት ምርት ከአለም ተወዳዳሪ የሌላት ማድረግ ተገቢ ነው እንዴ? ይህው አሁን በቅርቡ የሰማሁት አንድ አለማቀፍ ሪፖርት እንደሚለው ከሆነ ኢትዮጵያን ደስታ ከራቃቸው ቀዳሚ ሶስት ሀገሮች ውስጥ መድቧታል። ሪፖርቱን ቀለል ባለ ቋንቋ እንዘርዝረው ካልን ሀገራችን እምዬ ኢትዮጵያ ሀዘን ቤት ሆናለች እንደማለት ነው። አረ ምን ይሔ ብቻ ኢትዮጵያችን በሌላ ሪፖርት ላይ ደግሞ የግለሰቦችን መብት በማክበር ረገድ ከአንድ መቶ አስር ሀገሮች አንድ መቶ ስምንተኛ መሆኗ ተዘግቧል።
በርግጥ ባለፈው ግዜ እሳት የላሱት የኢቲቪ ህትመት ዳሰሳ አዘጋጆች ዘጋርድያንን ጠቅሰው በኢኮኖሚ እብደት ከአለም ሀገሮች አንደኛ ብሏታል ሲሉን ነበር። (ታይፕ ገድፊያለሁ መሰል በኢኮኖሚ እብደት ያልኩት እድገት ለማለት ፈልጌ ነው። ይሄ እድገት የሚሉት ቃል ዘላለሙን እብደት ከሚለው ጋር እንደተመሳሰለብኝ ልኖር ነው ማለት ነው?) በርግጥ የኢቲቪን ወሬ አብሮኝ ሲሰማ የነበረው ወዳጄ ሰዎቹ ሲተረጉሙ ተሳስተው ነው እንጂ ዘጋርድያን አንደኛ ያለን “በአትሌቲክስ ነው” የሚሆነው ብሎኛል። እኔም ለመንግስቴ በመቆርቆር ስሜት እንዴት እንዴት አትሌቲክስን የኢኮኖሚ እድገት ብለው ይተረጉማሉ? ብለህ ታስባለህ? ብዬ ብይዘው… ባለፈው ግዜ ወዳጃችን ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ላይ የቀረበበትን ማስረጃ አስታወሰኝ፤ እውነትም፤ ውቤ ለራሱ አባቱ ታመውበት ከውጪ ሀገር ለደወለለት ወንድሙ “ኦፕሬሽኑ ተካሂዷል። ገንዘብ ብትልክልኝ ደስ ይለኛል።” ብሎ ቢናገር ነው… ስልኩን የጠለፉት ጠላፊዎች “ኦፕሬሽን ያልከው የፖለቲካ ኦፕሬሽን ነው!” ብለው የተረጎሙት? እናም ይቺ የትርጉም ነገር እውነትም እኛ ዘንድ አታስተማምንም። (እኛ ተብሎ የተጠቀሰው የመንግስት ታማኞችን ነው… (ታማሚ አላልኩም!))
አፈር ስሆን ወዳጄ በጨዋታ መሀል ትዝ ብሎኝ ነው ከ ጋሽ ፍቅሩ ኪዳኔ “የፒያሳ ልጅ” መፅሐፍ ላይ ያነበብኳትን የቀድሞ ዘመን “ነጭ ለባሾች” ስራ ልንገራችሁማ… (ለዛሬ ዘመን ልጆች፤ “ነጭ ለባሽ” ማለት ደህንነት ወይም ሰላይ በአራዳ ቋንቋ “ሲለዩ” ማለት መሆኑን እነግራለሁ) እነሆ ጨዋታው በአዲስ መስመር…
አንዱ የጋሽ ይድነቃቸው ተሰማ አድናቂ የሆነ ወጣት በመጠጥ ቤት ውስጥ ሆኖ “ጋሽ ይድነቃቸውማ የሀገር መሪ የመሆን ብቃት ያለው ሰው ነው!” ብሎ ተናገረ። ይሄኔ ነጭ ለባሽ ሆዬ “ምን ሲደረግ ንጉሱ እያሉ ሌላ ሰው ለመሪነት ብቁ ነው ትላለህ?” ሲል አንገቱን አንቆ ወሰደው። ወጣቱ የጋሽ ይድነቃቸው አድናቂም “ባደነቅሁ ታነቅሁ” ብሎ ተርቶ፤ ከዛ ግዜ በኋላ መሳቀቅ ጀመረ። ሲሳቀቅ… ሲሳቀቅ አንድ ግዜ የመኪናው መሪ ተበላሽቶ ኖሮ፤ ጥግ አስይዞ ሊያቆማት መከራውን ሲያይ አንድ ወዳጁ ተመለከተውና ጠየቀው… “መኪናህ ምን ሆነችብህ?” ቢለው ግዜ “የኔ ጌታ ፖለቲካ አታናግረኝ!” ብሎ መለሰለት። አዎና እንዴት ብሎ “መሪው ተበላሽቷል!” ይበለው?
ሌላም አለ፤ በዛን ግዜ “ንጉስ” የሚባል ሲጋራ ነበር። አለ ጋሽ ፍቅሩ፤ ታድያ “ንጉስ” ሲጋራ በሱቁ የሌለው ነጋዴ “ንጉስ ስጠኝ” ሲሉት “ንጉስ የለም!” ብሎ ደፍሮ መናገር ይፈራ ነበር። ብሎ አጫውቶናል። (ጋሽ ፍቅሩ ላካፈለን የማይጠገቡ ጨዋታዎች ረጅም እድሜ ይሰጠው ዘንድ መርቀን እንቀጥላለን!)
ምን ብለን ነበር ወጋችንን ያቆምነው? እ… አዎ… ልማታዊ ጋዜጠኞቻችን በትርጉም ስህተት ይሁን “በማን ያገባዋል” ባይነት እንጃ በተለያየ ግዜ “አንደኛ ነን” ቢሉንም ሰዉ ግን “ስንተኛ እንደሆንን እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን” በማለት ዝም ብሏል። እየተባለ በከተማው ይወራል። አሉ።
የኔ ነገር አንዱን ስይዝ አንዱን ስጨብጥ እኮ የጨዋታችን ውል ሊጠፋብኝ ነው። ለነገሩ ወግ ምን ውል አለው…? ዝም ብለን እንቀጥልማ… እናልዎ ብሶት የወለደው ሰራዊት ዛሬም በርካቶችን ሆድ እያስባሰ ነው። በዚህም ጫካ ያለው ጫካ ገብቶ፤ ጫካ የሌለው ጫካ ገንብቶ “አረ በዛ!” ብሎ ትግሉን አጧጡፏል። በበኩሌ ሀገሬ ንግድ እንጂ በተለይ የነፍጥ ትግል እንዲጧጧፍባት አልፈልግም። (በቅንፍም “ነበር” እላለሁ) ነበር ስትል ምን ለማለት ፈልገህ ነው? ብሎ ወጥሮ የሚይዘኝ ካለ ለግዜው ዝርዝር ባይኖረኝም ባለፈው ሳምንት የፍትህ ወዳጃችን (እና አለቃችን) ተሜ ከጣፋት ውስጥ፤
“ምንም የማያውቀውን በሬ
ነካክተው ነካክተው አደረጉት አውሬ!”
ብሎ የከተባትን ግጥም እጋብዛለሁ። የምር ግን ወዳጄ መንግስታችን “በራሱ ላይ የታጋዮች ምልመላ እያከናወነ ነው።” የሚባል ነገር ሰምተዋል? አይ የሰሙ አይመስለኝም። እርስዎ የሰሙት ብሄረሰብ ለማመጣጠን ተብሎ እየተደረገ ያለውን የወታደር ምልመላ ነው። እኔ የምልዎት ደግሞ ሌላ ነው…! ለምሳሌ በዛን ሰሞን ርዮት አለሙን መርማሪዋ ቢላት ቢሰራት የሚፈልገውን አልናገር ብትለው ግዜ አይደለም እንዴ…”እንዲህ በአቋምሽ የፀናሽ ከሆንሽ ለምን ጫካ አተገቢም?” ብሎ ያላት! ታድያ ከዚህ የበለጠ ምልመላ የት ይገኛል። ይህንን የሰማ የርሷ አይነት አቋም ያለው ሁሉ እኮ ቆርጦ ጫካ መግባት ቢያቅተው፤ ልቡን ጫካ ውስጥ ደብቆ ኢህአዴግዬን “ልቤ አይስቅልሽም” የማለት እድሉ ሰፊ ነው። ታድያ ታጋይ መመልመል ማለት ይህ አይደለም? ቆይ እሺ ሰሞኑን በአዋሬ ገበያ ቤቶች መቃጠላቸውን ሰምተዋል አይደል? ታድያ… በቃጠሎው ቤት አልባ የሆኑትን ነዋሪዎች መንግስት ነብሴ “እናንተ ድሮውንም ህገወጦች ስለነበራችሁ ማደሪያችሁን ፈልጉ… ብሎ ፊት ነስቷቸዋል አሉ። እንኳን ሌላ ቀርቶ የተባረከው ቀይ መስቀል ድርጅት እንኳ፤ “ድንኳን ልስጣቸው” ቢል “አይመለከትህም አይኔ እያየ እነርሱ መጠለያ አያገኙም!” ብሎ መንግስት ተሟግቷል። ታድያ ይሄ በራስ ላይ ታጋይ ከመመልመል ውጪ ምን ይባላል። ራሱ ኢህአዴግን ጫካ አስገብተው ዛሬ መንግስት ያደረጉት እንዲህ እንዲህ አይነት ምክንያቶች መሆናቸውን የሚያስታውስ አንድ ባለስልጣን እንዴት ይጠፋል? ጎበዝ ይሄ የራስ ህመም ባለስልጠኖቻችን ላይ እየተጫወተባቸው ሳይሆን አይቀርም? እግዜር ሀኪሙን ይላክልን እንጂ!
የሆነ ሆኖ መንግስታችን ግማሹን ፊት ሲነሳ፣ ግማሹን ንብረት ሲነሳ፣ ግማሹን ድምፅ ሲነሳ ግማሹን… ብቻ በጥቅሉ በታጋይ ላይ ታጋይ እየጨመረ፣ እየጨመረ ዳግም በዛች ራድዮ ጣቢያ “የዘመናት ብሶት የወለደው…” ተብሎ ሲነገርባት ይታየኛል። ያለኝ አንድ ወዳጄ ነው።
እናልዎ… ኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ ግንቦት ሰባት ንቅናቄ፣ ኦጋዴን ነፃ አውጪ ሁሉም በየፊናው “ኢትዮጵያ የጋራ ቤታችን ናት” ሁላችንም ተከባብረን የምንኖርባት አዲስ ኢትዮጵያ እንመሰርታለን! ብለው እጅ ለእጅ ተያይዘዋል!” የሚለው ወሬ ዋና መነጋገሪያ ሆኗል። እርስዎ ይህንን ሲሰሙ ምን እንደተሰማዎት እንጃ…! በመንግስቴ ቤት ግን ጠላቶዎ ክው ይበልና ከሽብር የዘለለ “ክውታን” ፈጥሯል አሉ። እኛም እናንት አሸባሪዎች በተናጠል ያሸበራችሁት አንሶ በጣምራ መንግስትን “ክው” ታደርጉ ዘንድ ያስጨከናችሁ እንደምን ያለው ነው? ብለን ተደንቀናል።
በመጨረሻም 1
ቀዳማዊ እመቤት
የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ሰሞኑን አንድ ስልጣን አስረክበዋል። (ቆይ ቆይ አይደንግጡ…!) ስልጣኑ ምን መሰልዎ፤ “የአፍሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች የፀረ ኤድስ ክበብ ነበራቸው። የእርሱ ሊቀመንበር ደግሞ የእኛው እመቤት ነበሩ። ታድያ አሁን እርሱን ስልጣናቸውን ለናሚቢያው እመቤት አስረከቡ የሚል ወሬ ተነግሯል።
ይህ ዜና ሲነገር ምን ተሰማህ አይሉኝም? ይጠይቁኝ በሞቴ… እውነቱን ለመናገር ጥቃት ነው የተሰማኝ። ምን ሲደረግ ነው ስልጣን ለቀቁ የሚል ወሬ የምሰማው? ምንም ቢሆን እኮ የእሳቸው ሚስት ናቸው… እንደሚባለው ከሆነ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩም ይልቅ ቁጡ እና ሀይለኛ “ወንድ የሆነ ይነካኛል!” ባይ ናቸው… (አረ… በኔና በርሶ ብቻ ይቅር እንጂ ለርሳቸውም የሚመለሱ አይደሉም ሲባልም ሰምቻለሁ!) ታድያ እንዲህ ያሉት ሴት ስልጣን ለቀቁ ሲባል መስማቴ በእውኑ አስደንግጦኝ ነበር። ኋላ ላይ ግን ሳስበው አንድ ጥያቄ በአዕምሮዬ መጣ፤ እኔ የምልዎ ቀዳማዊነዎ… ሊቀመንበርነቱን ከለቀቁ በኋላ ሰላም ነዎት? እንደ ቀድሞ ይበላሉ? ይጠጣሉ? እንቅልፍም ይወስድዎታል? መልሱ “አዎ” ከሆነ እባክዎ ይሄንን ነገር ለክቡርነታቸውም ይንገሯቸው… “ሊቀመንበር ሳይሆኑ መኖር ይቻላል” ይበሏቸው። መልሱ “አይ” ከሆነ ግን በቸሩ መዳኒአለም ይዤዎታለሁ፤ ምንም እንዳይነግሯቸው!
በመጨረሻም 2
ሰማያዊ ፓርቲ
አዲሳባ ወጣት የነበር ጣት የሆኑ ፖለቲከኞች አንድ ፓርቲ አቋቁመዋል። ፓርቲያቸውም በምርጫ ቦርድ እውቅና አግኝቶ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተዋል። በነገራችን ላይ ይሄ ነገር ሊበረታታ የሚገባው ነገር ነው። አንዳንድ ወጣቶች የፖለቲካ ፓርቲ ሽሽት “ዴይ ፓርቲ” እያዘጋጁ ከህፃናት ተማሪዎች ጋር ሲደንሱ በሚውሉበት በዚህ ዘመን እንዲህ ሀገራዊ ራዕይ ይዞ ፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም ቀላል ነገር አይደለም።
እናልዎ… ይህ ሰማያዊ ፓርቲ በእንግሊዘኛ ሲጠሩት “ብሉ ፓርቲ” ይሉታል። ይህንን የሰማ ከወዳጆቼ ዋና የሆነው ምን አለኝ መሰልዎ… “እነዚህ ልጆች የአባላት ቁጥር እንዲጨምርላቸው ከፈለጉ ፓርቲውን “ብሉ” ብቻ ከሚሉት “ጠጡ” የሚልም ጨምረውበት “ብሉ ጠጡ ፓርቲ” ቢሉት ጥሩ ነበር።” ብሎኛል። የምር ግን ብሉዎች… እንግዲህ ስሙ አንዴ ወጥቷል ባይሆን ፕሮግራሙ ላይ ይጨመርበታ!
ይበሉ ወዳጄ በሚከተለው ምርቃት እንሰነባበት…
የሚያበላ የሚያጠጣ፣ ነገር የማያመጣ፣ ከሀገር የማያባርር፣ በጥበብ የሚያስተዳድር፣ ዘወር በል ሲሉት የሚሰማ፣ ያልሆነ ገገማ፣ ለህዝቡ የሚስማማ… እርሱ ጥሩውን መሪ ይስጠን… በትልቁ አሜን!
አማን ያሰንብተን!
Short URL: http://www.zehabesha.com/?p=3601

Post Reply

Return to “Jokes and Funny stuff ...ቀልዶች እና አዝናኝ ርዕሶች”