Page 1 of 1

‹‹የከተማው ‹አሽሟጣጮች› የግንቦት ሃያ ፍሬዎች ነን!›› አሉ : አቤ ቶኪቻው

Posted: 10 Jun 2011 08:56
by zeru

‹‹የከተማው ‹አሽሟጣጮች› የግንቦት ሃያ ፍሬዎች ነን!›› አሉ : አቤ ቶኪቻው

እሁድ ግንቦት 13 /2003 ዓ.ም አዲስ አበባ ደርቢ አኢትጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ትርጉም ያለው ጨዋታ ያደርጉ
ነበርና፣ ከተማችን አዲስ አበባ በዛን ሰሞን ከዘይት እና ስኳር ሰልፍ ቀጥሎ ታላቅ ህዝባዊ ሰልፍ አስተናገደች፡፡ ሰላሳ አምስት ሺህ ሰው የመያዝ አቅም ያለው አዲሳባ ስታድየም
በዙሪያው የተሰለፈውን ወፈ ሰማይ ህዝብ እን... ደምንም አጭቆ ካስገባ በኋላ ከውጪ የተረፈው ህዝብ ውስጥ የገባውን ይበልጣል፡፡ ኋላ ላይ ግን ‹‹ያልገቡ ብጹአን ናቸው›› የሚያሰኝ
አንድ አጋጣሚ ተከሰተ፡፡

ዝናብ! አደገኛ ዝናብ ሊዘንብ ያጉረመርም ጀመር፡፡ ‹‹ጉድ ፈላ!›› ስል የሰማችኝ አንዲት ሴት ‹‹አይዞህ አትስጋ ያልፋል፡፡›› አለችኝ ዘና ብላ፡፡ ነገሩ እንኳ
የሚያልፍ አይመስልም ግን ያልፋል ካለች ይሁን ብዬ እሺ አልኳት፡፡ እንደሰጋሁትም ዝናቡ ማካፋት ጀመረ! ልጅቷን ገልመጥ እያደረግሁ ‹‹የኛ ሜትሮሎጂ!›› ስል ላሽሟጥጣት
ሽቶኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ዝናቡ ትንሽ አካፍቶ አቆመ፡፡ ይሄኔ የልጅቷን ቅድመ ትንበያ የሰማ አንድ ወዳጄ እንዲህ ጠየቃት፡፡ ‹‹እባክሽ የኔ እመቤት ዝናቡ ያልፋል እንዳልሽው አለፈ!
ይሄ ክፉ ቀንስ እንዴት ነው የሚያልፍ ይመስልሻል…›› ሲል ጠየቃት፡፡ ልጅትም ቆፍጠን ብላ… ‹‹ትዕግስት ብቻ ነው የሚያስፈልገው ያልፋል!›› አለች፡፡ እኛም አሜን አልን!
ወዳጄ እንዴት ሰነበቱ… የዛሬው ጨዋታችን ተጀመረ! ‹‹እንዳያልፉት የለ ያ ሁሉ ታለፈ ታጋይ የህዝብ ልጅ በደሙ በላቡ ደማቅ ታሪክ ፃፈ!›› እያልን የምንዛፈንበት የአመቱ ግንቦት ሃያ
በመላው ሃገሪቱ ተከብሯል፡፡ ይህ ቀን የቻልን ጠምቀን እና ፈትፍተን ያልቻልን ሆ… ብለን ሰልፍ ወጥተን የምናከብረው ልዩ ቀን ነው፡፡ ስለዚህ እንኳን አደረስዎ ልበልዎታ! ሰልፉን
ተሰለፉ ወይስ እቤትዎ ቁጭ ብለው ‹‹የግንቦት ሃያ ፍሬ›› በሆነው ቴሌቪዥንዎ ሲከታተሉ ነበር! እኔ የምለው ወዳጄ… በቃ እዚህ አገር የተሰራው ስራ፣ እየተሰራ ያለው ስራ፣ ለመስራት
የታሰበው ስራ፣ እንኳንስ ሌላው ቀርቶ ልስራው… አልስራው… እያልን በአዕምሯችን የምናንሰላስለው ሁሉ የግንቦት ሃያ ፍሬ ሆነ አይደለም እንዴ! እንዲህ ነው እንጂ ካፈሩ አይቀር
አደራ ‹‹ፈ››ን እንዳያጠብቁብኝ! በነገራችን ላይ አንዳንድ ዋና የተባሉ ካድሬዎቻችን ልጆቻቸውን፣ ሚስቶቻቸውን እና ውሽሞቻቸውን ሳይቀር ‹‹የግንቦት ሃያ ፍሬ›› እያሉ በማሞካሸት
ለስርዓቱ ያላቸውን ታማኝነት በመግለፅ ላይ ይገኛሉ፡፡
የምር ግን ይቺ ነገር በተለይ ለፍቅር መግለጫ ጥሩ ትመስለኛለች፡፡ ፍቅረኛዎን ‹‹የሾላ ፍሬ ነሽ!›› የሚለውን ዘፈን ከመጋበዝ
ይልቅ ‹‹የግንቦት ሃያ ፍሬ ነሽ›› ቢሏት ለልጅቷም ላባወራውም ለድርጅታችንም የሚኖረው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፡፡ የአንዳንዱ ሰው ፍቅረኛ ደግሞ ከዚህ ውጪ ምርጫ ያላት አይመስልም፡፡ ቀጥሎ የተጠቀሰቺቱ ለዚህ ምሳሌ ትሆን ዘንድ እነሆ… ሰውየው ከፍቅር አቻው ጋር የተገናኘው ከድርጅታዊ ጉባኤዎች በአንዱ ነበር፡፡ ከእጅ አወጣጧ እስከ የታሸገ
ውሃ አጠጣጧ ድረስ ልብ ብሎ ተመለከታት፡፡ ወድያውም በፍቅሯ ተማረከ፡፡ በእውኑ ግንቦት ሃያ ባይመጣ ኖሮ ድርጅታዊ ጉባኤ ይኖር ነበርን?! አልነበረም፡፡ ድርጅታዊ ጉባኤ
ባይኖር ኖሮስ ለጥያቄ እጅ ማውጣት ወይም የታሸገ ውሃ በቄንጥ መጠጣት የሚሆን ነገር ነበር…? በፍጹም አይደረግም ነበር፡፡
ታድያ እነዚህ ሁሉ ባይኖሩ ኖሮ ይህ ሰው ፍቅሩን ያገኛት ነበር…? ኧረ ከየት ብሎ! ካላችሁ በትክክል መልሳችኋል፡፡ እናስ ይቺ ሴት ለባለታሪካችን ‹‹የግንቦት ሃያ ፍሬ!›› ከመሆን ውጪ ምን ምርጫ አላት… ምንም! ያው እንግዲህ እንደሚታወቀው ሰሞኑ የግንቦት ሃያ ፍሬዎች በመላው ኢትዮጵያ እየተሰበከ ያለበት ወቅትም አይደል…? እናልዎ በቴሌቪዥን የብሄር ብሄረሰብ ሙዚቃዎች የግንቦት ሃያ ፍሬ መሆናቸውን ‹‹የሚያሳምን›› ዝግጅት እየተከታተልን ነበር፡፡ ታድያ እነ ሰለሜ ሰለሜ እነ ዙምባራ እነ ሚሶ ሚሶ እነ ኮበለይ… እነ ወዘተ እየተዘፈኑ እኒህ ሁሉ የግንቦት ሃያ ፍሬ መሆናቸው ተነገረን፡፡ እኛ ትጉሃኖች በኋላ ድንገት ጥያቄና መልስ ውድድር ላይ ‹‹የግንቦት ሃያ ፍሬ ከሚባሉ ሙዚቃዎች አስሩን ጥቀስ… ስንባል ግር እንዳይለን ማስታወሻ እየያዝን ሳለ አንዱ አቋረጠንና ‹‹እኔ የምለው እነዚህ ዘፈኖች ግንቦት ሃያ ፍሬ ናቸው የሚባሉት የዜማ እና ግጥሙ ደራሲ መንግስት ነው እንዴ?›› ብሎ ጠየቀን፡፡
እንደዚህ አይነቱን ጠያቂ ምን ይሉታል? ‹‹የሚጠይቀውን አያውቅምና… ይቅር በሉት!›› ብሎ ከመለማመን ውጪ! ወዳጄ የምር ግን የግንቦት ሃያን ሰልፍ እንዴት አዩት… እኔማ በሰልፈኛው ብዛት ተደምሜ አስር አስር ጊዜ ‹‹ወይ ድንቅ… ወይ አጀብ… ወይ ጉድ… እንደው ይሄ ሁሉ በስንት ቀን እንዲህ ተቀናጀ… ይገርማል!›› እያልኩ ሳደንቅልዎ አንድ ወዳጄ ሰማኝና ‹‹ተው ባክህ ብዙ
አትገረም!›› አለኝ፡፡ እንዴት ባክህ…? ብለው ‹‹ይህ የምትመለከተው ሰልፈኛ ቀድሞ በየቀበሌው በዘይትና በስኳር ሰልፍ ልምድ የቀሰመ ነውና ምንም አይደንቅም!›› አለኝና
አረፈው፡፡ ወዳጄ ሰዉ እንዴት እንዴት እንደሚያናግረው ሰሙልኝ! ይሁን እስቲ…! ስለ ዘይት ለኮፍ ካደረግን አይቀር ከተማዋን በዘይት ለማጥለቅለቅ መንግስታችን ቆርጦ መነሳቱን
የሰማነው በግንቦት ሃያ ዋዜማ ላይ ነበር፡፡
እናልዎ የዘይት ስርጭቱ ነገር እንደተጀመረ… (እንደው በቢሮ ቋንቋ እናውራ ብለን እንጂ ስርጭቱ ከምንል የዘይት እርጭቱ ብንል ይሻላል
መሰል!) ታድያ ያኔ በቴሌቪዥናችን ውዳሴ መንግስት ሲነበብልዎ አንድ ወዳጄ ሰማና ምን አለን መሰልዎ… ‹‹ይሄ ነገር መጀመሪያ ከምድረ ገፅ ያጠፋው ሌላ መንግስት ነበር እንዴ?››
ሲል ጠየቀን፡፡ የምር ግን አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎቻችን ቃለ መጠይቅ ከማድረጋቸው በፊት መጠነኛ ምክር ቢሰጣቸው መልካም ይመስለኛል፡፡
እንዴ አንዳንዶቹ እኮ ዛሬ ዘይት መምጣቱን የሚያመሰግኑ እየመሰሉ የሚናገሩት ንግግር እኮ ቀድሞ መንግስት ያልነበረ ነው ያስመሰሉት፡፡ የሆነ ሆኖ ዘይትና ስኳርን በተራጨን በማግስቱ ግንቦት ሃያ ሆነ!
በቴሌቪዥኑም በራዲዮኑም የግንቦት ሃያ ፍሬዎች ተሰበኩ፡፡ ዘይት እና ስኳርን ጨምሮ የግንቦት ሃያ ፍሬ ናቸው ተባለ፡፡ (በቅንፍ ዘይትና ስኳር የግንቦት ሃያ ፍሬ የሚሆኑት ሲረክሱ
ሲረክሱ በገበያው ሲገኙ ሲገኙ እንጂ ሲጠፉ የነጭ ለባሾች ሴራ ወይም የሻቢያ ተላላኪ ሃይሎች ሸፍጥ መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው፡፡) በነገራችን ላይ ስኳር ስኳር ስል ትዝ ያለኝ… ስካርም
የግንቦት ሃያ ፍሬ መሆኑን አንድ አስተያየት ሰጪ ሲናገር ሰምቻለሁ፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪው ከሆነ ለበርካታ ጊዜያት ስካርም ሆነ ስኳር በዋዛ የሚገኙ አልነበሩም፡፡ ይኸው ከዘንድሮ
ገና ዋዜማ ጀመሮ ቢራ ተመን ወጣለት ይኽው ድሮ በብስጭት ብቻ ስንሰክር የነበርን ሰዎች ቢራ መጎንጨት አልፎም መስከር ጀመርን፡፡
ታድያ ግንቦት ሃያ ባይኖር ኖሮ ተመን ከየት
ይመጣል? ተመን ባይመጣ ቢራ ማን ሊጠጣ ቢራ ባንጠጣ ስካር ባዳችን አልነበረም?›› ሲል ተናግሯል፡፡ ይናገር ይህ ንግግር ራሱ የግንቦት ሃያ ፍሬ መሆኑን ማን በነገረው? አሁን
አሁን ደግሞ የከተማው አሽሟጣጮች የግንቦት ሃያ ፍሬዎች ነን እያሉ ይገኛሉ፡፡ እንዴት… ችግር ባይኖር… ኑሮ ውድነቱ ባይመጣ… ገንዘባችን ዋጋ ባያጣ… ባይኖር ይሄ ሁሉ ጣጣ
አሽሟጣጭ የሚባል ይኖር ነበርን? በእውነቱ አሽሟጣጮች የተወለዱት ከዚህ ውስጥ ነውና አሽሟጣጮች የግንቦት ሃያ ፍሬዎች ነን!! እያሉ ይገኛሉ፡፡
አሽሟጣጮቹ አክለው ሲገልጹ
‹‹እኛ አሽሟጣጮች ባለፈው ፋሽስታዊ ስርአት ማንነታችን ተዋርዶ፣ ተጨቁነን፣ ተበድለን፣ ያለንበት ተረስቶ ነበር፡፡ ይኸው ዛሬ ግን ፀሐይ ወጣልን!›› ሲሉ ግንቦት ሃያን
አንቆለጳጵፀዋል!! በመጨረሻም ሰለሞን ተካ ሁሉም ዜሮ ዜሮ እያለ ሲዘፍን የነበረው ሰለሞን ተካ አሁን ደግሞ ‹‹ሁሉ መቶ መቶ እያለ እየዘፈነ ነው፡፡ ግንባታውም መቶ፣ አመራሩ
መቶ፣ ዴሞክራሲው መቶ፣ ጥጋባችን መቶ… ሁሉም መቶ መቶ… አደረገው መቶ ግንቦት ሃያ መጥቶ!!›› አይነት ይዘት ያለው ዘፈን እየዘፈነ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም በተለይ
በዕለተ ግንቦት ሃያን ሰለሞን ተካን የቴሌቪዥኑ ‹‹ስክሪን ሴቨር›› አድርገውት አልፏል፡፡ ታድያ ዘፈኑን በተደጋጋሚ የሰማው አንድ ወዳጃችን ሰውየውን ልብ ብሎ ካየው በኋላ
የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል፡፡ ‹‹ይህ ሰው ጫፍ ካልያዝክ አትኖርም ተብሏል እንዴ… ባለፈው ዜሮ ዜሮ አለን… አሁን ደግሞ መቶ ከመቶ ሰጠን ምናለ ቀስ ቀስ እያለ እንኳ
ቢጠጋን! የሚታዘብ ሰው የላቸውም ተብሏል እንዴ… !›› ብሏል፡፡ የምር ግን ይቺ ጫፍ የመያዝ ነገር እኔም አልተመቸችኝም! ጫፍ መያዝ ለመውደቅ መዘጋጀት ማለት ነው፡፡
እና ሰለሞን ተካ ራሱን በመሀሉ ቢተካ መልካም ይመስለኛል፡፡
ለዛሬ ከማብቃቴ በፊት አንድ ምርቃት እነሆ… ‹‹ክፉ ቀንም ክፉ ሰውም እስኪያልፉ ፅናቱን ይስጠን!››

አማን ያገናኘን!